ዘለንስኪ ከቡድን ሰባት ሃገራት ጋር ዛሬ ይወያያሉ 

Ukraine

Ukraine

የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ቮልደሚየር ዘለንስኪ በዛሬው ዕለት በአለም ዓቀፉ ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ከሚያሳርፉት ከቡድን ሰባት አባል ሃገራት ጋር ይወያያሉ።

የብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች በዚህ ዓመት በየካቲት ወር ዩክሬን ወደ ጦርነት ከገባች በኋላ ድጋፋቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሃገራቱ በቢሊዮን ዶላሮችንም ወደ ዩክሬን በመላክ ወታደራዊ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ዛሬ የሚካሄደው የአባል ሃገራቱ ስብሰባም ሩሲያ ሶቪየት ሕብረት ናዚ ጀርመን ያሸነፈችበትን 77ኛውን የድል በዓል ለማክበር በዋዜማው ሳለች ነው። ይህ የድል በዓል በመላው ሩሲያ በየዓመቱ በከፍተኛ ወታደራዊ ትዕይንት ይከበራል። ይህን ተክትሎም የዩክሬን ባለስልጣናት ሩሲያ ነገ ሰኞ የድል በዓሏን አክብራ ስታበቃ ከባድ የቦምብ ጥቃት ልታደርስ ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ትላንት ማምሻውን ዘለንስኪ በካርኪቭ የሚገኘው የዝነኛው ገጣሚ እና ፈላስፋ ሪሆሪ ስኮቮሮዳስ ስም የተሰመውን ሙዚየም ላይ ሩሲያ ያደረሰችውን ጥቃት አውግዘዋል።

የዩክሬን ባለስልጣናት ሰኞ ዕለት ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን ውስጥ በሚገኝ አንድ ት/ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት 60 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። በቦታው ሌሎች 30 ሰዎችን ማዳን የተቻለ ሲሆን ተጨማሪ 2 አስክሬኖች ተገኝተዋል።

በኪየቭ የምትገኘው የአሜሪካ ድምጿ ዘጋቢ አና ቼርንኮቫ በማሪፖል የብረት ፋብሪካ ተከበው የነበሩ ሴቶች፣ ሕጻናት እና አዛውንቶች ሁሉም ቦታውን ለቀው መሄዳቸውን ዘግባለች። ይሁን እንጂ የነፍስ አድን ጥረቱን ከአለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት ጋር በመሆን እየመራ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስካሁን ድረስ የተልዕኮውን ማብቃት አላረጋገጠም።

በተያያዘ ዜና በምስራቃዊ ዩክሬን ሩሲያ በፈጸመችው የቦምብ ጥቃት በት/ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ 90 ሰዎች ሞተው ሊሆን እንደሚችል ተፈርቷል። ለሳምንታት በዘለቀው የሩሲያ እና የዩሬን ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ጦርነት የተካሄደበት የሉሃንስክ አውራጃ አስተዳዳሪ ከቢልሆርቪስካ 30 ሰዎችን ማዳን ቢቻልም ሌሎቹ ት/ቤቶች ግን ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።