ዩናይትድ ስቴትስ የሶማሊያን የዲሞክራሲ ሂደት በሚያደናቅፉ ተጨማሪ ሶማሊያውያን ላይ የቪዛ ዕገዳ ጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን ትናንት ረቡዕ ባወጡት መግለጫ የሶማሊያ መንግሥት የምክር ቤታዊ ምርጫ ሂደቱን ከትናንት በስተያ ማክሰኞ እአአ መጋቢት 15 ሊያጠናቅቅ ራሱ ያወጣውን ቀነ ገደብ ተግባራዊ ሳያደርግ መቅረቱን ተከትሎ የዲሞክራሲ ሂደቱን በማደናቀፍ ተጠያቂ ወይም ተመሳጣሪ ናቸው በተባሉ ተጨማሪ ሰዎች ላይ የቪዛ ማዕቀብ እርምጃ ወስጃለሁ ብለዋል።
ብሊንከን በመግለጫቸው አስከትለውም ምንም እንኳን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት አበረታች እርምጃ የታየ ቢሆንም አሁንም ያልተያዙ ከሠላሳ ስድስት በላይ ክፍት የምክር ቤት መቀመጫዎች እንዳሉ አመልክተዋል።
የምርጫው ሂደት መዛባት እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን የሚደግፉ እና ሂደቱ ግልጽ እንዲሆን የሚጥሩ ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የወከባ የእስር እና የጥቃት ዒላማ እየተደረጉ መሆኑን የሚያመለክቱ ተዓማኒ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ቀጥለዋል ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።