ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ በዩክሬን ሆስፒታል መደብደቧን አወገዘች

  • ቪኦኤ ዜና

በጥቃቱ የተጎዳው የማዋለጃ ሆስፒታል ማሪፖል፣ ዩክሬን እአአ መጋቢት 7/2022

ዋሺንግተን የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ማሪፖል ከተማ የሚገኝ የማዋለጃ ሆስፒታል ላይ ጥቃት አድርሰዋል የሚለውን ሪፖርት አውግዛለች፡፡ በአንጻሩ ፖላን የሩሲያ ሰራሽ የጦር ጄቶች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የአየር ኃይል በኋላም ወደ ዩክሬን እንዲገቡ የማድረግ እቅድ ማቅረቧን ዩናይትድ ስቴትስ አልተቀበለችውም፡፡

የፔንታገን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ “ሉዓሏዊ ሃገራቱ ለራሰቸው ማድረግ የሚፈልጉትን በራሳቸው መወሰን ይችላሉ፤ ነገር እነዚህን ጄቶች ወደ እኛ ይዞታ አምጥተን በኋላም ወደ ዩክሬን ማዛወሩ ግን በአሁኑ ሰዓት የምናስበው አይሆንም” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ “አውሮፕላኖችን ከዩናይትድ ስቴትስ የአየር ሰፈር አንስቶ ወደ ጦር ቀጠና ማብረሩ የእኛም ሆነ የኔቶ ፍላጎት ለምን እንዳልሆነ መረዳት ግልጽ ነው ለዚህ የጦር ባለሞያ መሆን አያሻም” ብለዋል፡፡

የዩክሬን የሆስፒታል ጥቃትን ተክትሎ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልዴሚየር ዘለንስኪ ኔቶ በዩክሬን የአየር ኃይል ውስጥ ምንም ዓይነት በረራ እንዳይኖር እንዲከለክል በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግርም “ኃይሉ አላችሁ ነገር ግን ሰብዓዊነት ያጣችሁ ትመስላላችሁ” ብለዋል፡፡