ዩናይትድ ስቴትስ ለአማራ እና ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች የሚደርስ አስቸኳይ ዕርዳታ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

ዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላላ መጠኑ 250 ሜትሪክ ቶን የሚሆን ሰብአዊ አቅርቦ ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት - አይኦኤም የኢትዮጵያ ጽ/ቤት እና ለኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን ልትለግስ መሆኑ ተዘገበ።

የዕርዳታ አቅርቦቱ ዩናይትድ ስቴትስ በአማራ እና አፋር ክልሎች በቀጠለው ግጭት ለተጎዱ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ ድጋፍ የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑን ከአዲስ አበባው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ይፋ የተደረገ ዘገባ አመለከት።

አምባሳደር ትሬሲ ኤ ጃኮብሰን የአደጋ ጊዜ አቅርቦቱን ለአይኦኤም የኢትዮጵያ ቢሮ ተጠባባቂ ኃላፊ ሚስተር ጂያን ዣኦ እና ለኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን የምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ሁሴን ከነገ በስቲያ ረቡዕ በሚከናወን የርክክብ ሥነ ስርዓት እንደሚያስረክቡ ታውቋል።