በዘገባዎች የወጡ ዩክሬን ውስጥ አሉ የሚባሉ የዘር መድልዎ አድራጎቶችን አሜሪካ አወገዘች

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

“ማንኛውም የዘር መድልዎ፤ በተለይ በቀውስ ውስጥ የሚደረግ ይቅር የማይባል ነው” ሲል የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

ከቃል አቀባዩ ዛሬ የወጣው መግለጫ ስለ እንዲህ ዓይነት አድራጎቶች የሚድያ ዘገባዎችን መመልከቱን ጠቁሞ የዩክሬን ጎረቤቶች ዓለምአቀፍ ከለላ ለሚፈልጉ ሁሉ ድንበሮቻቸውን ክፍት በማድረግ መቀጠላቸውን መሥሪያ ቤቱ እንደሚያደንቅ አመልክቷል።

ድንበር አቋርጦ ጎረቤት ሃገሮች የሚገባ እያንዳንዱ ሰው በእኩል ዓይነት መስተናገዱንና ያለበት ሁኔታ በሚጠይቀው መሠረት የሚገባውን ድጋፍ ማግኘቱን ለማረጋገጥ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሥፍራው ላይ ካሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን የቃል አቀባዩ መግለጫ ተናግሯል።

መግለጫው አክሎም የአካባቢው ሃገሮች ስደተኞችን በሚመለከት የገቧቸውን ግዴታዎችና ስደተኞችን ወደ መጡበት በኃይል ያለመመለስ “ነን-ረፉልሞ” መርኆችን እንዲያከብሩ ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታበረታታ ገልጿል።

ከሁከት እየሸሹ ያሉ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል ያለቪዛ የመንቀሳቀስ መብት ለሌላቸው የሦስተኛ ሃገር ዜጎች ዩክሬን መውጣት እንድትፈቅድላቸው፣ ጎረቤቶቿም እንዲያስገቧቸው ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታሳስብ መግለጫው አመልክቷል።