የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቩላድሚር ዚለንስኪ ራሽያ በቤላሩስ ድንበር ላይ ተገናኝተው ለመነጋገር ያቀረበችውን ጥያቄ ዛሬ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ቢቀበሉም ራሽያ ከምዕራብ ሀገራት ጋር ያላት መካረር በመቀጠሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን የኑውክሌር መቃወሚያ ሀይላቸው በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የኔቶ አባላት የሀይል መግለጫ እያወጡ መሆኑና በራሽያ ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ መጣላቸው ለውሳኔያቸው ምክንያት መሆኑን ፑቲን አስታውቀዋል።
ውሳኔውን አስመልክቶ ለኤቢሲ ዜና ምላሽ የሰጡት የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ፓስኪ በበኩላቸው ከኔቶም ሆነ ከዩክሬን የተደቀነ ማስፈራሪያ እንደሌለ በመግለፅ ራሽያ ጥቃቷን ለመቀጠል የሌለ ስጋት እየፈጠረች ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የራሽያ ጦር የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪቭ እና ሌሎች ከተሞችን ለመቆጣጠር ከዩክሬን መከላከያ ሰራዊት ጋር የሚያደርገው ውጊያ አራተኛ ቀኑን ይዞ እንደቀጠለ ነው።
የራሽያ ጦር ዛሬ ካርኪቭ ወደ ተሰኘው የዩክሬን ሁለተኛ ትልቁን ከተማ የገባ ሲሆን በስፍራው ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑንና ራሽያ ከተማዋን መቆጣጠር እንዳቃታት የዩክሬን ዋና አቃቤ ህግ የሆኑት ኢሪና ቬንዲክቶቫ ገልፀዋል።
ራሽያ በበኩሏ ከሽብርተኛ የተቃጣ ስጋትን ለማጥፋት ባለችው ጦርነት ድል እያገኘች መሆኗንና 821 የዩክሬን ወታደራዊ ተቋማትን፣ 87 ታንኮችንና ሌሎች ኢላማዎችን ማውደሟን አስታውቃለች።
የምዕራብ ሀገር አጋሮች ለዚለንስኪ የእርዳታ ጥሪ ምላሽ መስጠታቸውን የቀጠሉ ሲሆን አዲሱ የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በትላንትናው እለት 1ሺህ የታንክ አምካኝ መሳሪያዎች እና 500 ሚሳይሎችን እንደሚልኩ የተናገሩ ሲሆን ፈረንሳይም የመከላከያ መሳሪያዎች እና ነዳጅ እንደምትልክ አስታውቃለች።