ሆንግ ኮንግ ውስጥ ኮቪድ -19 በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ ነው

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከትሎ የፊት እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያደረጉ ታካሚዎች በሆንግ ኮንግ ሆስፒታል

የ98 ዓመቷ ላም ፉን ሆንግ ኮንግ ከሚገኘው ካሪታስ የሕክምና ማዕከል መግቢያ ላይ በተዘጋጀ የሆስፒታል አልጋ ላይ ከሱፍ የተሰራ ብርድ ልብስ ተጀቡነው የኮቪድ-19 ማጣሪያ ምርመራ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

“በጣም ጥሩ ስሜት አይሰማኝም” ሲሉ ነበር አፍና አፍንጫቸው በጭምብል እንደተሸፈነ እና የፊት መከለያ እንዳጠለቁ እያነጋገራቸው ላለው የሮይተርስ ዘጋቢ የገለጡት።

ላም ባለፈው ሃሙስ በካሪታስ ሆስፒታል የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ በተዘጋጀ ሥፍራ ላይ እንዲቆዩ ከደረጉ በርከት ያሉ ታካሚዎች አንዷ ናቸው። በኮውሉን ባሕረ ገብ መሬት በሼንግ ሻ ዋን ወረዳ የ400 ሺህ ሰዎች የሚኖሩ አብዛኛው ከሰራተኛው መደብ የሆኑ ሆንግ ኮንግ ዜጎችን የሚያገለግል ሆስፒታል ከአፍ እስከ ገደፉ በመሙላቱ ሊቀበሉና ሊያስገቧቸው ባለመቻላቸው ነበር በዚያ ሁኔታ ባሉበት ለመርዳት የተገደዱት።

እየዘነበ ባለው ዝናም መሃል የአካባቢው የሙቀት መጠን ወደ 15 ዲግሪ ሴልሺየስ ዝቅ ብሏል።

የህክምና ባለሙያዎች ላም በዚያ ሁኔታ ለምን ያህል ጊዜ መጠበቅ እንዳለባቸው መንገር አልቻሉም። የመጀመሪያው ምርምርራ የኮሮቫይረስ በሰውነታቸው መኖሩን የታየ ሰዎች ህክምናው ከመጀመሩ በፊት ተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራ ማድረግ አለባቸው።

ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሆስፒታል አልጋዎች ኮቪድ-19 ህሙማን በተያዙባት ዓለም አቀፏ የፋይናንስ ማዕከል በሥፋት የሚስተዋሉት መሰል ትዕይንቶች የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ስርዓቷ እንደምን ባለ ከፍ ያለ ጫና ውስጥ መሆኑን ከሚሳዩ ምልክቶች ውሥጥ ናቸው።

በአንድ ወቅት ባብዛኛው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተከለለች ተደርጋ ትታይ የነበረችው ሆንግ ኮንግ አሁን የከተማይቱን ልዩ ልዩ ክፍሎች ያዳረሰ አዲስ ዙር ወረርሽኝ በመጋፈጥ ላይ ናት። የንግድ ድርጅቶች በበኩላቸው ለመጣው ፈተና እየተሰናዱ ሲሆን አንዳንዶች መንግስት “ዜሮ ኮቪድ” በሚል የሚያራምደው ፖሊሲ የተሰላቹ እና ትዕግስት እያጡ ይመስላሉ።

በአቅራቢያው በሚገኘው ከሰራተኛው ክፍል የሆኑ ነዋሪዎች የሚበዙበት ሻም ሹዪ ፖ የተባለ አካባቢ ያሉ አንዳንድ የመኖሪያ መንደሮች እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው ቤቶች ከተቀረው አካባቢ ተለይተው ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። ቀድሞ በሸማጦች ተጨናንቀው የሚታዩት የገበያ ማዕከሎች እና የመንገድ ዳር ገበያዎች አሁን ብዙም ሰው አይታይባቸውም። በአንድ ወቅት መተላለፊያ የሚታጣባቸው “ዳይ ፓይ ዶንግ” የሚባሉት ደምበኞቻቸውን ከቤት ውጭ ክፍት በሆነ ሥፍራ ያስተናግዱ የነበሩት መብል ቦታዎች እና ጌጣ ጌጥ መሸጫዎች ለዓይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ጸጥ ይላሉ።

ይህ ሁሉ ለውጥ እየታየ ባለበት "መንግሥት ሁኔታውን ቀለል አድርጎ ወስዶታል” ሲሉ ለሚታየው የሆስፒታል መኝታዎች፣ የሕክምና ቁሳቁሶች እና የባለሞያዎች እጥረት ባለሥልጣናቱን የሚከሱ አሉ።

“ነገሮች ከዚህም እየከፉ ሊሄዱ ይችላሉ” የሚል ስጋት ያላቸው ነዋሪዎች በአካባቢው ቁጥራቸው የበዛ አረጋውያን መኖራቸውን እና ብዙዎቹም ያለመከተባቸውን ይናገራሉ።

7.4 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ከተማ በሚያገለግሉ ሆስፒታሎች ለተፈጠረው አስከፊ ሁኔታ የሆንግ ኮንግ ባለስልጣናት በትላንትናው ዕለት ይቅርታ ጠይቀዋል።

የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ሥርዓቱ ከአቅሙ በላይ በመጨናነቁ የተነሳ ባለስልጣናት ቀደም ሲል የበሽታው ምልክት የሌላቸው አለያም ቀላል ህመም ያለባቸውን ሰዎች ሳይቀር ወደ ህክምና ተቋማት ወይም የለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንዲላኩ የሚያደርገው “ዜሮ-ኮቪድ” በመባል የሚታወቀውን የከተማይቱ ፖሊሲም ለማስተካከል ተገደዋል።

ወረርሽኙ የከሰተው ምስቅልቅል የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው የፊታችን ሰኔ ወር በሚያበቃው በሆንግ ኮንጓ መሪ ኬሪ ላም ላይም ተጨማሪ ጫና መፍጠሩ ተዘግቧል።