ዩናይትድ ስቴትስ ለየትኛውም ወገን እንደማታዳላ ሳማንታ ፓወር ገለጹ

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር

በርካታ ኢትዮጵያውያን እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ለሕወሓት እንደሚወግኑ በመግለጽ ላይ ቢሆኑም፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ውንጀላውን አጣጥለዋል፡፡ ፓወር በትናንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ያደረጉትን የአንድ ቀን ቆይታ ተከትሎ በሰጡት መግለጫ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ አገልግሎት ተደራሽነት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ፓወር ለእርዳታ የተዘጋጀ ክምችት ለተቸገሩ ወገኖች እንዲደርስ መንግሥት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ለዕርዳታ አቅርቦቶች መስተጓጎል ሕወሓትን ተጠያቂ ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፣ ሕወሓት ከድርጊቱ ከተቆጠበ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ለመታደግ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይነት የሰብዓዊ አገልግሎት በአግባቡ እንዲደርስ ካስፈለገ ሕወሓት ከጻብ- ጫሪ ድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባ ወ/ሮ ሙፈሪያት የገለጹ ሲሆን ፓወር በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ ለማንም ወገን ሳታዳላ የሰብዓዊ መብት እና የዓለምአቀፍ ሕግጋትን መርሆች የሚጥሱ አካላትን መጠየቋን እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ እና ግጭቱን የሚያባብሱ ንግግሮች መቆም እንዳለባቸውም ፓወር አሳስበዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ጋር በዚሁ ጉዳይ የተወያዩት ፓወር፣ ከተደራሽነት አንጻር ውስን መሻሻሎች ቢኖሩም የሚጠበቀው ለውጥ እንዳልመጣ ተናግረዋል፡፡

“ተደራሽነቱ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት በሐምሌ አጋማሽ ላይ፣ ወቅታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት በየሳምንቱ ከ500 እስከ 600 የዕርዳታ አቅርቦቶችን የያዙ የጭነት መኪኖች ወደ ትግራይ መግባት እንዳለባቸው መግለጹን ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ባለው መረጃ የዕርዳታ አቅርቦት የጫኑ 153 መኪኖች ወደ ትግራይ መግባት ችለዋል፡፡ እንደተመድ ከሆነ ከሀምሌ አጋማሽ እስከ ነሓሴ 2 መግባት የነበረባቸው 1500 የጭነት መኪኖች ናቸው፤ የገባው ግን 153 ነው፤ ይህም ከሚፈለገው 10 በመቶ ነው፡፡ ስለዚህ የአሠራር ሥርዓት ለውጥ መኖሩን ተመልክተናል፤ ለምሳሌ የወረቀት ሥራዎች ተስተካክለዋል፤ ፍቃድ ለመስጠት የሚወስደው ጊዜም በወረቀት ላይ መሻሻሉን አይተናል፡፡ ነገር ግን በችግር ላይ ለሚገኙ ሰዎች የምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለማድረስ ባለው መዘግየት ላይ ተስፋ የምናደርገውን ለውጥ እያየን አይደለም፡፡” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ከፍተኛ የእርዳታ አህል ክምችት መኖሩን የገለጹት የተቋሙ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፣ ይህ ለእርዳታ የተዘጋጀ ክምችት ለተቸገሩ ወገኖች እንዲደርስ መንግሥት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ለእርዳታ አቅርቦቶች መስተጓጎል ሕወሓትን ተጠያቂ ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፣ ሕወሓት ከድርጊቱ ከተቆጠበ መንግስት የትግራይን ሕዝብ ለመታደግ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል በሁሉም አቅጣጫ በሮች እንደተዘጉበት የሚገልጸው ሕወሓት በበኩሉ፣ በአሁኑ ወቅት ውጊያ በማድረግ ላይ የሚገኝበት አንዱ ምክንያት ለክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚገባበትን በር ለመክፈት እንደሆነ ራሳቸውን ከሕወሓት ኃይል መሪዎች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የሰብዓዊ ቀውሶችን ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ ግጭቶችን ማቆም እንደሆነ የሚገልጹት ሳማንታ ፓወር፣ በግጭቱ የሚሳተፉ ኃይሎች ግጭቱን በማቆም እርቅ ለመፍጠር እና በአጎራባች ክልሎች ከያዟቸው ይዞታዎች ለመውጣት ውይይት እንዲጀም ጠይቀዋል፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ዩናይትድ ስቴትስ ከማንም ጋር የመወገን ፍላጎት እንደሌላትም ገልፀዋል።

ከእናንተ እና ከመንግስታችሁ ጋር ያለን ግንኙነት በተለያዩ እሴቶች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እንደምንፈልግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንድታውቁ እፈልጋለሁ፡፡ በግጭት ወቅት አንድን አካል ለመምረጥ ወይም ለማዳላት አይደለም፡፡ እነዚህ እሴቶች ለውስጣዊ ግጭት ወታደራዊ መፍትሔ የለም፤ ሁሉም አካላት ግጭት በማቆም አስቸኳይ የተኩስ አቁም ለማድረግ በመስማማት እርቅ ለማድረግ እና ወታደሮችንና ሚሊሻዎችን ከአጎራባች ክልሎች ለማስወጣት ንግግር እንዲጀምሩ የሚሉ ናቸው፡፡ በትግራይ የተጀመረው ግጭት እየተስፋፋ መሆኑን አሜሪካ በከፍተኛ ስጋት እየተመለከተች ነው፡፡ አሁን ላይ በአፋር 76 ሺህ በአማራ ደግሞ 150 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ እንገምታለን፡፡ ብለዋል።

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልም መንግሥት አወጅኩ ካለው የተናጥል ተኩስ አቁም በኋላ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ሕወሓት በከፈታቸው ጥቃቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን መፈናቀላቸውን ገልጸው፣ የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ጨምሮ የተርዓዶ ድርጅቶች እነዚህን ተፈናቃዮችም ሊደርሱ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ በአፋር እና አማራ ክልሎች ለተፈናቀሉ ሰዎችም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ የተቋሙ አስተዳዳሪ ፓወር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ተፈናቃዮችን ፍላጎት እንዴት ማሟላት እንዳለብን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረናል፡፡ በሕወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተፈናቀሉትን ማለቴ ነው፡፡ በችግር ላይ የሚገኙ ንጹኃን ኢትዮጵያውያንን መርዳት እንፈልጋለን የዩኤስኤይድ እና አጋሮቻችን የምንሰራው ይሄንኑ ነው፡፡” ብለዋል።

በቀጣይነት የሰብዓዊ አገልግሎት በአግባቡ እንዲደርስ ካስፈለገ ሕወሓት ከጻባ- ጫሪ ድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባ ወ/ሮ ሙፈሪያት የገለጹ ሲሆን ፓወር በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ ለማንም ወገን ሳታዳላ የሰብዓዊ መብት እና የዓለማቀፍ ሕግጋትን መርሆች የሚጥሱ አካላትን መጠየቋን እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ እና ግጭቱን የሚያባብሱ ንግግሮች መቆም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

“ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ንግግር ውጤቱ ውጥረትን ማባባስ ብቻ ነው፣ እንዲሁም በታሪክ ብዙውን ጊዜ ብሔር ተኮር የጭካኔ ድርጊቶችን ያስከትላል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ ምታቀርበው ውይይት እንዲደረግ እና ግጭት እንዲቆም ነው፡፡ ግጭት አባባሽ ንግግሮች እየተባባሱ ሲሄዱ ወደድርድር የመምጣት ነገርም ይበልጥ ፈታኝ እየሆነ ይሄዳል፡፡”

በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይከሰት፣ የተሟላ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ ተደራሽነት እንዲኖር ለማስቻል በመንግስት ላይ ግፊት የመፍጠር ዓላማን አንግበው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሳማንታ ፓወር፣ ከጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋርም የተወያዩ ሲሆን ለጤና እና ለሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፍ የሚውል ተጨማሪ 45 ሚሊዮን ዶላር ፈንም ይፋ አድርገዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የመገናኘት ዕቅድም የነበራቸው ፓወር፣ በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ካለመኖራቸው ጋር በተያያዘ ሊያገኗቸው እንዳልቻሉም ገልጸዋል፡፡

(ዘገባው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ድምፅ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ዘጋቢ ኬኔዲ አባተ ነው)