የስፖርት ዜናዎች

ሰለሞን ቱፋ ደምሴ

ጃፓን እያስተናገደችው ባለው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሀገራትን የወከሉ ስፖርተኞች ስማቸውን በክብር መዝገብ ላይ ለማስፈር ፉክክራቸውን ቀጥለዋል። በስፖርታዊ መድረኩ ኃያላን የነበሩት ሀገራት ዘንድሮም የሜዳሊያ ሰንጠረዡን እየመሩ ይገኛሉ። ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ሰዓት ጃፓን የመሪነቱን ክብር ከዮናይትድ ስቴትስ ተረክባለች። አዘጋጇ ጃፓን በ8 ወርቅ በ2 ብር በ3 ነሃስ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎች ዓለምን ስትመራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በ 7 ወርቅ በ 3 ብር እና በ4 ነሃስ በአጠቃላይ በ14 ሜዳሊያዎች ትከተላለች። ቻይና በ6 ወርቅ በ5 ብር እና በ7 ነሃስ በአጠቃላይ በ18 ሜዳሊያዎች በ3 ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከአፍሪካ አህጉር እስካሁን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው ሀገር ቱኒዚያ ብቻ ናት። በወንዶች 400 ሜትር ነጻ ዋና ውድድር አህመድ ሃፍናዊ ለሀገሩም ሆነ ለአህጉሪቱ የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኝቷል። ጄክ ማክሊን ከአውስትራሊያ፣ ኪሪያን ስሚዝ ከዩናይትትድ ስቴትስ የብር እና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

***

ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሁለት ስፖርቶች ተወዳዳሪዎቿን አሳትፋለች። በ58 ኪሎግራም ቴኳንዶ ስፖርት የተሳተፈው ሰለሞን ቱፋ ደምሴ በመጀመሪያ ዙር ጃፓናዊውን ሰርጂዮ ሱዙኪን ማሸነፍ ቢችልም በቀጣይ ባደረጋቸው ውድድሮች ተረትቷል። በአጠቃላይ ከ15 ተፋላሚዎች መካከል 7ኛ ደረጃን በማግኘት ውድድሩን በአበረታች ደረጃ አጠናቋል። የዚህ ዘርፍ አሸናፊ ጣልያናዊው ቪቶ ዴላኪዊላ ሆኗል። የብር ሜዳሊያውን ሞሃመድ ካሊል ከቱኒዚያ ፣ የነሃስ ሜዳሊያውን ደግሞ ጃንግ ጃን ከደበቡ ኮሪያ ወስደዋል።

ትናንት በተደረገው የሴቶች የጎዳና ብስክሌት ግልቢያ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረችው ሰላም አምሃ ውድድሩን አቋርጣለች። ኦስትራዊታ አና ኪሶኖፈር ፣ ኔዘርላንዳዊቷ አኔሜክ ቫን ቭለውተን እንዲሁም ጣልያናዊቷ ኤልሳ ሎንጎ የወርቅ ፣ ብር እና ነሃስ ሜዳሊያውን ወስደዋል።ውድድሩ 22.1 ኪሜትርን ማካለል ይጠይቃል።

***

በመካሄድ ላይ ባለው ኦሎምፒክ ከተመዘገቡ ያልተጠበቁ ውጤቶች መካከል አንዱ የህልም ቡድን ተብሎ የሚጠራው እና እውቅ ተጫቾችን ያሳለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ቅርጫት ኳስ ቡድን በፈረንሳይ አቻው መሸነፉ ይጠቀሳል። ቡድኑ 83 ለ76 ተሸንፋል። በኦሎምፒክ ታሪክ ከጎረጎሳዊያኑ 2004 ወዲህ 17 ዓመት ውስጥ የዮናይትድ ስቴትስ ቡድን ሽንፈት ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው ነው።