“ዋነኛው ውጤት ኃይል አመንጭተን ለሕዝባችን ኤሌትሪክ ስናቀርብ ነው” ዶ/ር ስለሺ በቀለ

ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የፌስቡክ ገፅ ላይ በስክሪን ቅጂ የተወሰደ

ሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዛሬ ከቀትር በፊት ተጠናቋል። ግድቡ ሞልቶ ውሀው በአናቱ ላይ ሲፈስ በስፍራው ተገኝተው የተመለከቱት የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ ሁለተኛው ሙሌት መጠናቀቁ በሁለት ተርባይኖች ኃይል ለማመንጨት እንደሚያስችል ተናግረዋል። የክረምቱ ዝናብ ከፍተኛ መሆኑ ግድቡ በፍጥነት እንዲሞላ ማስቻሉንም የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ በኋላ እስከ ሦስት ወራት ባሉት ጊዜያት የሚኖረው ቀጣይ ሥራ ኃይል ማመንጨት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በንግግራቸውም “ሁለተኛው ሙሌት በሁለት ተርባይኖች ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገንን የውሃ መጠን ሙሉ ለሙሉ መያዝ አስችሎናል። ይህ በራሱ ትልቅ ውጤት ቢሆንም ዋነኛው ውጤት ግን ኃይል አመንጭተን ለሕዝባችን ኤሌትሪክ ማቅረብ ነው። ስለዚህ በቅርብ ጊዜ የእርሱንም ብስራት አምጥተን የምናደርስ መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ” ብለዋል።

ግድቡ እስካሁን ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋን ቢያስቀርም ከሙሌቱ በኋላ ባለው የክረምት ጊዜ በተለይ ሱዳን የጎርፍ አደጋ እንደሚያሰጋት አብራርተው፣ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ግድቡ እንደሚጠቅማቸው በመረዳት በመልካም ጉርብትና ለመኖር መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በግድቡ ጉዳይ በሦስቱ ሀገራት መካከል ያለው አለመግባባት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ የሁለተኛው ሙሌት መሳካት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት የሚያስችል እንደሆነ በርካታ የዘርፉ ምሑራን ይስማማሉ፡፡

(ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

Your browser doesn’t support HTML5

“ዋነኛው ውጤት ኃይል አመንጭተን ለሕዝባችን ኤሌትሪክ ስናቀርብ ነው” ዶ/ር ስለሺ በቀለ