ስድስተኛ ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለአንድ ዓመት ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ። ለስኬታማነቱ የበርካታ አካላት የጋራ አስተዋጽዖ ወሳኝ ሚና እንደነበረው የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል አስታውቀዋል። በድሬዳዋና ሐረር ጉብኝት ያላኬዱት ወይዘሮ ሙፈሪያት ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም አጠባበቅ ውጤት እያሰገኘ ነው ብለዋል።
የአንዳንዶችን ስጋት ባስቀረ ሁኔታ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በሰላም ለመጠናቀቁ መንግሥት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ሆኖም የኅብረተሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ቦርድና የመገናኛ ብዙሃን ሚናም ወሳኝነት እንደነበረው የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በተለይ ለቪኦኤገልጸዋል። ከዚህ ተሞክሮ ለቀጣይ ምርጫዎች ትምሕርት ለመቅሰምም ጥናት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በድሬዳዋና ሐረር የሰላምና በጎ ፈቃድ ስራዎች ሁኔታን ለመከታተል ድሬዳዋ መጥተው የነበሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለምርጫው ሰላማዊነት ትልቁን ድርሻ የሰጡት ለሕዝቡ ነው።
ከኅብረተሰቡ ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከምርጫው በፊት አራተኛ ዙር ውይይቶችን በማድረግ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ያረጋገጡት ነበር ብለዋል። ይሁንና በኅብረተሰቡም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ይህ አቋም እንዲያዝበማድረገ ረገድ ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸው የራሱ አስተዋጽዖ እንዳለው ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት የሚያምኑት።
ካደረጉት ቅድመ ዝግጅት አንጻር ምርጫው ሰላማዊ እንደሚሆን ከሞላ ጎደል ግምቱ ቢኖርም የሕዝቡ ጨዋነትን ግን ከጠበቁት በላይ እንዳገኙት ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት የሚናገሩት።
ድሬዳዋ ላይ በነበራቸው ቆይታ በሥነምግባራቸው የተመሰገኑና የታመኑ ገለልተኛ የሕዝብ ተወካዮች በምርጫው ተዓማኒነት ላይ የላቀ ሚና እንደነበራቸው መረዳታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
ገለልተኛና ተዓማኒ የሕዝብ ተወካዮችን የማደራጀት ሥራን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ13 ሺ ቀበሌዎች ተግባራዊ ማድረጋቸውንም ለቪኦኤ ገልጸዋል። ይህ መደረጉ ከምርጫው ባሻገር ወንጀል በመቀነስ፣በከተሞች ሰላም በማስከበር እና ነዋሪው ምርታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድም ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው እየታየ ነው ብለዋል። ከገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ባሻገር ማህበረሰብ ተኮር ፖሊሳዊ አገልግሎትን በመዘርጋት ውጤት እየተገኘበት ነው ብለዋል። ለዚህም ድሬዳዋን ለአብነት ጠቅሰዋል
ወይዘሮ ሙፈሪያት በድሬዳዋ ቆይታቸው ከድሬዳዋ አስተዳደር የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ አመራሮችና ከጸጥታ ሃይሎች ጋርም ምክክር አድርገዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰልጥነው በመላ ሃገሪቱ ከተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋርም በድሬዳዋና ሐረር ከተሞች ችግኝ የተከሉ ሲሆን ወጣቶቹየድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችን በሚደግፉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽዖም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
Your browser doesn’t support HTML5