የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በኅዳሴ ጉዳይ ተነጋገረ

  • ቪኦኤ ዜና

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ

በሱዳን እና በግብፅ ጥያቄ በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ለመነጋገር ዛሬ ሐሙስ ስብሰባ የተቀመጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት የሃገሮቹን መከራከሪያዎች አዳምጧል።

ኢትዮጵያ “የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ የፀጥታ ሳይሆን የልማት በመሆኑ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሊቀርብ አይገባውም፤ ምክር ቤቱም ሊነጋገርበት አይገባም” ስትል የቆየች ሲሆን፤ በስብስሰባው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ፊት ለፊትበውኃ ጉዳይ የቀረቡ ምናልባት የመጀመሪያ ሚኒስትር ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተናግረዋል።

ዶ/ር ስለሺ አክለውም ግድቡ ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት እንዲውል መሥራት የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን አመልክተው እየተገነባ ያለውም በኢትዮጵያውያን በራሳቸው ሃብትና ላብ መሆኑንንም ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።

ኅዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ያለውን ትርጉም ሲናገሩ፤ “ግድቡ ከአረብ ሃገሮች በዳዶ እግራቸው እየተባረሩ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ነፃ ያወጣል” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ስብሰባው በጥቅሉ ፍትኃዊነት የጎደለውና ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ለምክር ቤቱ የተናገሩ ሲሆን ይህንኑ ጠቅሶ የወጣውን የድርጅቱን ትዊት በግል የትዊተር ገፃቸው ላይ ማምሻውን አስተጋብተዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ለምክር ቤቱ ያሰሙትን ረዥም ንግግር የጀመሩት፤ “የመቶ ሚሊዮን ነፍሶች ሃገር አሁን እየታየ ባለ አደጋ ላይ ነች” ብለዋል።

“ይህ ግዙፍ ግድብ እያደገ በሄደና እያንዳንዱ ጡብ በተጨመረ ቁጥር ከግድቡ በታች ያሉ የሚሊዮኖች ሚስኪኖች ሕይወት የወደፊት እጣ ፋንታ ጥቁር ጥላ እየለበሰ ይሄዳል” ብለዋል።

ሳሜህ ሹክሪ አክለውም፤ “ኢትዮጵያ ጅረቱ ኃይቅ ሆኗል አባይ የኛ ነው እያለች በወንዙ ላይ ለምታደርገው ጥቃት የግብፅ ምላሽ ትዕግስት እና ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት ወይም ማንም የማይጎዳበት የተካከለ ሁኔታ እንዲሰፍን የሰላም መንገድን መከተል ሆኖ ቆይቷል።” ብለዋል።

ንግግሮቹን ያደመጠውና የተወያየው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በአመዛኙ ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት እንዲያዝ ወዳደላ አዝማሚያ አዘንብሏል። የፀጥታ ምክር ቤቱ በሕዳሴ ጉዳይ ላይ እየተነጋገረ ባለበት ሰዓት ከዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ እንደዚሁም ከኒውዮርክ አካባቢያዊ ግዛቶች የተጠራሩኢትዮጵያውያን ለግድቡ መገንባት ያላቸውን ድጋፍ አሰምተዋል።

(በነገው ምሽት የሟላ ዘገባ ይዘን እንመለሳለን)