የብሊንከን የአውሮፓ ጉብኝት

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን በአውሮፓ አይሁድ ላይ በናዚዎች ጭፍጨፋ መካሄዱን የሚያስተባብሉትን እና ጸረ ሴማዊነትን በጋራ ለመታገል መስማማታቸው ተገለፀ።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ቃል ይህ የጋራ ጥረት ያሁን እና መጪ ትውልዶች በአይሁዶች ላይ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ እንዲያውቁ እና ከዚያ ታሪክም ትምህርት እንዲማሩ ያገለግላል ብለዋል።

ብሊንከን ዛሬ በርሊን በሚገኘው የተፈጁት የአውሮፓ አይሁድ መታሰቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር ጭፍጨፋውን መካድ እና ጸረ ሴማዊነት ጸረ ተመሳሳይ ጾታ አፈቃሪነት፥ የውጭ ሃገር ሰው ጠልነት ዘረኝነትን በመሳሰሉት አድልዎኛ አመለካከቶች ሰልፍ ገብተዋል፥ የዲሞክራሲ ስርዓቶቻችንን ለማፍረስ ለሚፈልጉት ደጋፊ ማሰባሰቢያ እየሆኑ ነው" ብለዋል።

አስከትለውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ስለአይሁድ ጭፍጨፋ ታሪክ የምናስተምርበት አዳዲስ ዘዴዎች መፍጠር የሚያስፈልገን በዚህ ምክንያት ነው። ስላለፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዛሬውን እና የወደፊት ጉዞአችንን አቅጣጫ ለማስያዝም ጭምር ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከጀርመኑ አቻቸው ሃይኮ ማስ ጋር ይህንኑ አጋርነት የተመለከተ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ቀደም ብሎ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን በርሊን ላይ ከተካሄደው የሊቢያ ዘላቂ ሰላማዊ መንግሥት ምስረታ ንግግር ተከትሎ ጉባኤውን ተከትሎ ከሊቢያ የሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዳባይባ ጋር ተነጋግረዋል።

ትናንት ረቡዕ በርሊን ላይ ጀርመን እና የተመድ ባስተናገዱት የሊቢያ ጉባኤ ላይ የአስራ ሰባት ሃገሮች ባለሥልጣናት የተካፈሉበት ሲሆን በሀገሪቱ በመጪው ታህሳስ ወር ብሄራዊ ምርጫዎች እንዲካሄዱ ድጋፋቸውን አጠንክረው ገልጸውበታል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ባወጡት መግለጫ "ባዕዳን ሃይሎች እና ቅጥረኛ ተዋጊዎች በሙሉ ሃገሪቱን በፍጥነት ለቀው መውጣት እንዳለባችው ያስታወሱ ሲሆን በዚህ ነጥብ ላይ ቱርክ ቅሬታ አሰምታለች

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን የቱርክን ቅሬታ በተመለከተ ሲናገሩ ቱርክ ሊቢያ ውስጥ አባላቴ የሚገኙት የት መድ ድጋፍ ካለው የቀድመው የሽግግር መንግሥት ጋር ባለኝ ሥምምነት ሥልጠና ለመስጠት የገቡ ናቸው እንደምትል አስረድተዋል።

የሊቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከበርሊኑ ጉባዔ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል የባዕዳን ሃይሎች መውጣትን በሚመለከት በንግግሩ እርምጃዎች ተመዝግበዋል። በቀጣዮቹ ቀናት በሁለቱም ወገኖች በኩል ያሉት ባዕዳን ቅጥር ወታደሮች ይወጣሉ ብለን ተስፋ እንደርጋለን ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣኑም ይህ ርምጃ እጅግ አስፈላጊ ነው። አሁን ተግባራዊ መሆን አለበት ብለዋል።