የቡድን ሰባት አባል ሃገሮች መሪዎች ጉባኤ

  • ቪኦኤ ዜና

የሰባቱ ባለጸጋ ሃገሮች ማኅበር ቡድን ሰባት አባል ሃገሮች መሪዎች እንግሊዝ ካርቢስ ቤይ ያካሄዱትን ጉባኤ ለድሆች ሃገሮች ከአንድ ቢሊዮን በላይ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመለገስ ቃል በመግባት እንዲሁም ቻይናን በተለያዩ ጉዳዮች በመንቀፍ ትናንት ዕሁድ አጠናቀዋል።

መሪዎቹ በጉባኤቸው ማብቂያ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት እና ዓለም አቀፍ ተግባር በሚል ርዕስ ባወጡት የጋራ መግለጫ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይም አትኩረዋል። በክልሉ የሚካሄደው ግጭት መቀጠሉ እንዲሁም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ለረሃብ አደጋ የሚያጋልጥ የከበደ ሰብዓዊ ቀውስ መደቀኑን የሚገልጹት ሪፖርቶች በጥልቅ አሳስበውናል ብለዋል።

በማስከተልም የሚፈጸመውን መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃት ጨምሮ የሚደርሱት አስከፊ የጭካኔ አድራጎቶች እናወግዛለን ያለው የቡድን ሰባት መሪዎች የጋራ መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮምሺነር ቢሮ በጉዳዩ ላይ የማጣራት ስራዎቹን መቀጠሉን እንደግፋለን ብለዋል። ትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋል በተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሙሉ ተጠያቂነት መኖር አለበት። ፈጻሚዎችም ህግ ፊት እንዲቀርቡ እናሳስባለን ብለዋል።

በክልሉ የሚካሄዱ ግጭቶች ባስቸኩዋይ እንዲቆሙ፣ ሰብዓዊ ረድዔት ለሁሉም አካባቢዎች ያለምንም እንቅፋት ተደራሽነቱ እንዲመቻች እና የኤርትራ ወታደሮች በአስቸኳይ ከክልሉ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል። ላሉት ቀውሶች ብቸኛው መፍትሄ ተዓማኒ የሆነ የፖለቲካ ሂደት ነው ያሉት የቡድን ሰባት መሪዎች ሁሉም ወገኖች ይህንኑ መንገድ እንዲከተሉ እናሳስባለን ሲሉ አክለዋል።

አስከትለውም የኢትዮጵያ መሪዎች የዜጎች ሁሉ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች መከበርን መስረት ያደረገ ብሄራዊ እርቅና መግባባትን የሚያራምድ በይበልጥ ሰፋ ያለ አሳታፊነት ያለው የፖለቲካ ሂደት እንዲከተሉ በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።