የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ እስራኤል እና ሃማስ በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ አሳሰቡ፤ በግጭቱ የሚገደሉት ሰዎች እና በንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት ተባብሷል።
በአረብ ሃገሮች በሙስሊም ሃገሮች ጥያቄ ዛሬ በተከፈተው የተመድ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ዋና ጸኃፊው ባሰሙት ንግግር "ከሁሉም በላይ ደጋግሜ የምማጸነው ሁለቱ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ ነው” ብለዋል።
ከቁጥጥር ውጪ የሚሆን ድንበር ተሻጋሪ የፀጥታ እና የሰብዓዊ ሁኔታ ቀውሶች እንዳይፈጠር ለመከላከል በአፋጣኝ ግጭቱ መብረድ ይኖርበታል ያሉት ዋና ጸኃፊው "ጦርነትም ህግ አለው፥ በመጀመሪያ ደረጃ የስቪሎች ደኅንነት መጠበቅ አለበት" ሲሉ አሳስበዋል።
"በምድር ላይ ገሃነመ እሳት ካለ፣ እሱ ዛሬ የጋዛ ህጻናት ያሉበት ሁኔታ ነው" ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱን ወገኖች ወደኋላ እንዲመለሱ እና ሁለት ሃገሮች ጎን ለጎን የሚኖሩበትን ብቸኛ የሰላም አማራጭ ለማንቀሳቀስ እንዲሰሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያግዛቸው ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ቁጥራቸው ወደ አስራ ሁለት የሚደርስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉባኤው ላይ ለመገኘት ወደኒው ዮርክ የሚጓዙ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ወርረሽኝ ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በአካል ስብሰባ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።
ዲፕሎማቶቹ እየተወያዩ ባሉበት በዛሬው ዕለትም ሁለቱ ወገኖች ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች ያካሄዱ ሲሆን የእስራኤል አውሮፕላኖች ጋዛ ከተማን እንዲሁም ዲየር አልባላህ እና ካን ዩኒስ ከተሞችን በቦምብ ደብድበዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ የእስራኤልን እና የፍልስጥኤምን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ወደአካባቢው ተጉዘዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ሃገራቸው ጋዛ ላይ የምታደርሰውን የቦምብ ድብደባ በእጅጉ እንድትቀንስ ያቀረቡትን ጥሪ ውድቅ አድርገው ግባችንን እስከምንመታ እንቀጥላለን ብለዋል።
ኔታንያሁ ባወጡት መግለጫ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ስለሚሰጡን ድጋፍ በእጅጉ አመሰግናለሁ፤ ይሁን እንጂ እስራኤል ለዜጎችዋ ሰላም እና ጸጥታ እስከሚመለስ ወደፊት ትገፋለች ብለዋል።
እስከትናንት ረቡዕ ማታ ድረስ በግጭቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ጋዛ ውስጥ 227 እንደደረሰ የጋዛ የጤና ባለሥልጣናት ገልጸዋል። እስራኤል በበኩሏ አስራ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉባት አስታውቃለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን የእስራኤሉን አቻቸውን ቤኒ ጋትዝን ትናንት ለሁለተኛ ጊዜ ማነጋገራቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን እስራኤል ራሷን ከጥቃት የመከላከል መብት እንዳላት በድጋሚ አረጋግጠው የንጹሃን ህይወት መጥፋትም በእጅጉ የሚያሳስብ መሆኑን ለእስራኤሉ አቻቸው በድጋሚ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አመልክተዋል።