“የጸረ ኮቪድ ክትባታቸውን አሟልተው የተከተቡ ሰዎች ከቤት ውጭም ሆነ በቤት ውስጥ በአብዛኛው ያለ ፊት መሸፈኛ ጭምብል መንቀሳቀስ ይችላሉ” ሲል የዩናይትድ ስቴትሱ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ ባለፈው ሳምንት መገባደጂያ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ አሜሪካውያን መመሪያው በህይወታቸው ላይ በተጨባጭ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ በመመዘን ላይ ናቸው።
ከዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው የሚሆነው ብቻ ነው፡ አሟልቶ የተከተበው። አንድ አራተኛው ያህሉ ደግሞ ካሉት ሶስት የተለያዩ ክትባቶች አንዱን ለመውሰድ ያለማሰቡን ነው በተደጋጋሚ የተደረጉ የድምጽ ማሰባሰቢያ ጥናቶች ያመላከቱት። ለዚህም ይመስላል አሜሪካውያን፥ የንግድ ድርጅቶች እና የጤና ባለሥልጣናት፤ ይህ ሁሉ ባለበት የዩናይትድ ስቴትሱ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ከጥቂት ገደቦች በስተቀር “ክትባቱን ሙሉ በሙሉ የወሰዱ ግለሰቦች የፊት መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ መንቀሳቀስ ይችላሉ” የሚለውን መመሪያ ማውጣቱ ድንገት ያልተጠበቀ እርምጃ የሆነባቸው።
ዶ/ር ሮሼል ወለንስኪ የዩናይትድ ስቴትሱ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ ድሬክተር ናቸው። መመሪያው በአጭሩ “ስለ ግለሰብ ኃላፊነት ላይ ነው” ይላሉ።
“የተከተቡ እና ያልተከተቡ ሰዎች ማንነት ስለማይለይ” በሚል ነበር አንዳንድ የህዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሞያዎች መመሪያውን በጣም ድንገተኛ እና ግራ የሚያጋባ ሲሉ የተቹት፡፡
በአንጻሩ የባይደን አስተዳደር በበኩሉ የተከተቡ ሰዎችን ለመለየት በሚል አንዳንዶች የሚያነሱትን የክትባት ፓስፖርት የሚል መጠሪያ የተሰጠውን መለያ አልፈጥርም ሲል ካሁን ቀደም ይፋ አድርጓል።
አዲሱ የሲዲሲ መመሪያ ታዲያ የንግድ ወይም የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች እና ሌሎች ክትባት የተከተቡትን ካልተከተቡት ለይተው እንዲያውቁ ያግዛል የተባለውን መታወቂያ መሰል የክትባት ካርድ አስመልክቶ ዳግም ሞቅ ያለ ውይይት ቀስቅሷል።
ዋለንስኪ እንደሚሉትም መመሪያው የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን ጨርሶ ስለማስወገድ ሳይሆን፤ እያንዳንዱ ሰው ጤንነቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል ነው።
“ላልተከተቡ ሰዎች ግን” አሉ ዲሬክተሯ .. “ላልተከተቡ ሰዎች ግን መመሪያው አልተለወጠም።”
ባለፈው ሳምንት መገባደጂያ የፊት መሸፈኛ ጭምብላቸውን ሳያደርጉ ከምክትላቸው ካማላ ሃሪስ ጋር ብቅ ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሻሻለውን የCDC መመሪያ “ለአሜሪካ ታላቅ ቀን ነው” በማለት ነው የገለጹት፡፡
የዩናይትድ ስቴትሱ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከሉ መመሪያም በአንጻሩ በመላው አገሪቱ `አንዳች ለውጥ ማስከተሉ አልቀረም። አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ክትባቱን የወሰዱ ሸማቾችን የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንዲያጠልቁ መጠየቅ አቁመዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ መመሪያውን መገምገም በቀጠሉበት የቀደሙትን ሕጎች ይዘው መምረጣቸውን እየተናገሩ ነው።
ቁጥራቸው አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ አባላት ያሉትን የምግብና የችርቻሮ ድርጅቶች ሠራተኞችን የሚወክል አንድ ማህበር አዲሱ መመሪያ አባላቱን ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል” ሲል ሥጋቱን ጠቁሟል፡፡
ድሬክተሯ ግን ቀጣይ ያሉትን እና ድርጅቶቹ እንዲወስዱ የሚጠብቋቸውን እርምጃዎች ያብራራሉ።
ታዲያ ሁሉም ግዛቶች አይደሉም ህጎቻቸውን ፈጥነው ለማላላት የተዘጋጁት። የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን አድርጎ መገኘት እና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ አሁንም በአውሮፕላን እና በሌሎች የሕዝብ ማመላለሻዎች ግድ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ግዛቶች እና የንግድ ተቋማት የማህበረሰቦቻቸውን ወደ ቀድሞው ይዞታቸው መመለስ ለመርዳት ነፃ የባቡር ትኬቶችን መስጠት፤ ቢራ መጋበዝ እና የገንዘብ ጉርሻ ቢጤ እስከመስጠት የሚደርሱ ያልተከተቡ ሰዎች እንዲከተቡ ለማበረታታት የታለሙ አዳዲስ ዘዴዎችን እያስተዋወቁ ነው።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5