አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት መልካም ግንኙነት እንዲቀጥል ትፈልጋለች - አምባሳደር ዴቪድ ሺን

በኢትዮጵያና በቡርኪናፋሶ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ሀገር ጆርጅ ዋሽንግተን ዩንቨርስቲ የውጭ ግንኙነቶች መምህር የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሺን

በኢትዮጵያና በቡርኪናፋሶ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ሀገር ጆርጅ ዋሽንግተን ዩንቨርስቲ የውጭ ግንኙነቶች መምህር የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሺን

የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ እንዲያስቆምና ክልሉን መልሶ ለመገንባት እንዲችል ዩናይትድ ስቴትስ እየጣረች መሆኑንና ያንን ለማድረግ የሚያስችል የማማከርና የሰብዓዊ ርዳታ እየሰጠች መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። አምባሳደር ሺን ይህን ያሉት ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብፅ እና ሱዳን መንግስታት ጋር ለመነጋገር ልዩ መልዕክተኛ መላኳን ማስታወቋን ተከትሎ ነው።

Your browser doesn’t support HTML5

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት መልካም ግንኙነት እንዲቀጥል ትፈልጋለች - አምባሳደር ዴቪድ ሺን

(ዝርዝሩንከላይ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ)

ቀደም ሲል በኢትዮጵያና በቡርኪናፋሶ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ሀገር ጆርጅ ዋሽንግተን ዩንቨርስቲ የውጭ ግንኙነቶች መምህር የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሺን ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵይና ኤርትራ ጋር ባላት ግንኙነትና በተለይ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ግጭት አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ ሚና ምን እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚኖረው ሰላም መስፈን ኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ሀገር መሆኗን ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታምን አስረግጠው የተናገሩት አምባሳደር ዴቪድ ሺን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ እንደማትፈልግ ተናግረዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ ሀገሪቱ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ እንድታሻሽልና የዲሞክራሲ እንቅስቃሴዎች እንዲበረታቱ ለማድረግ የሚያግዛትን ፖሊሲዎች የምትከተል ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስን ጥረት በመጥፎ አይን እንድታየው የሚያደርግ ነገር ማድረግ አትፈልግም።"

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያሳደረች ያለው ጫና ሀገሪቱን ወደ ቻይና ፊቷን እንድታዞር ሊያደጋት ይችላል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ሺን ሲመልሱ፡

"አሳሳቢው ነገር ኢትዮጵያን ወደ ቻይና የመግፋቱ ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ችግሮች እንዲወገዱ ማድረግና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካና የምዕራብ ሀገራት አጋር ሆና በሱዳንና ሶማሊያ ሰላም የማስከበር ስራዋን እንድትቀጥል ማድረግ ነው።"

ሌላው ለዴቪድ ሺን የቀረበላቸው ጥያቄ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አለመውጣታቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ከኤርትራ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ምን ሊመስል እንደሚችልና በአምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን የሚመራው የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ቡድን ወደ ኤርትራ መጓዙ ምን ሚና ይኖረዋል የሚል ነው። ዴቪድ ሺን በምላሻቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከአመታት በኃላ አምባሳደር ፌልትማንን ወደ ኤርትራ መላኳ አበረታች መሆኑን ገልፀው፣ ኤርትራ በትግራይ ክልል ውስጥ ምን እያረገች እንደሆነ በግልፅ ይነጋገራሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝብ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ መኖራቸውን ይቀበላሉ ብዬ አላስብም። ይሄ ሉዓላዊነትን የሚፈታተን ነው። ስለዚህ ወታደሮቹ በአስቸኳይ ወደ ኤርትራ መመለሳቸው የኢትዮጵያም፣ የአሜሪካም፣ የኤርትራም ፍላጎት ነው። የማይመለሱ ከሆነ ዩናይት ስቴትስ ኤርትራን በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተቀባይነት የሌላት ሀገር አርጋ ልትቆጥራት ትችላለች። "

ዴቪድ ሺን ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቻይና በጅቡቲ ወደቦች ላይ የጦር አይሮፕላኖቿን ማሳረፍ የሚያስችላትን ይዞታ እያስፋፋች መሆኑና በአጠቃላይ ዓለም አቅፍ የጦር አቅሟን ለመገንባት የምታደርገው ጥረት በዩናይትድ ስቴትስ ላይ በሚፈጥረው ስጋት ላይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ዩናይትድስቴትስ የቻይናን እንቅስቃሴዎች በቅርበት እየተከታተለች ነው ያሉት ሺን ቻይና ዓለም አቀፍ የጦር ሀይሏን ለማሳደግ በምታደርገውን እንቅስቃሴ ዙሪያ የበለጠ ግልፅ ትሆናለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።