ህንድ በዛሬው ዕለት 314,835 አዲስ የኮሮናቫይረስ ተያዦች መገኘታቸውን አስታወቀች። ከአንድ ዓመት በላይ በአስቆጠረው ዓለም አቀፍ ወረርሺኝ በዚህ ደረጃ በአንድ ቀን በየትኛውም ሃገር ተመዝግቦ እንደማያውቅ ተገልጻል። በንፅፅር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባለፈው እአአ ጥር ሁለት ቀን የተገኙት 300,310 እንደነበሩ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲው የወረርሺኙን ይዞታ የሚከታተለው ማዕከል ያሳያል።
ህንድ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በከባዱ እየተዛመተ ባለው የቫይረስ ስርጭት የተነሳ የጤና ጠበቃ ሥርዓቷን በእጅጉ ያዳከመ ሲሆን ሆስፒታሎች እየሞሉ እና የከበደ የኦክሲጂን እጥረት መፈጠሩም ተገልጿል።
የኦክሲጂኑ እጥረት ከመበርታቱ የተነሳ የዋና ከተማዋ የኒው ዴሊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማዕከላዊው መንግሥት በየኢንዱስትሪዎች ለተለያዩ ስራዎች የሚውል ኦክሲጂን ወደሆስፒታሎች እንዲዛወር እንዳያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ህንድ ውስጥ የቫይረሱ ስርጭት የበረታው አንድም በይበልጥ በሚዛመተው የቫይረሱ ዝርያ ምክንያት እንዲሁም ወረርሺኙ ከጥቂት ወራት በፊት ጋብ ያለ በመሰለበት ጊዜ የነበሩት የእንቅስቃሴ እገዳዎች በመነሳታቸው እንደሆነ የጤና ጥበቃ አዋቂዎች ይናገራሉ።
በዓለም ዙሪያ ባሁኑ ወቅት ያለው የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች ቁጥር ከ143 ሚሊዮን 813 ሺህ 870 ማለፉን የሞቱት ሰዎች ቁጥርም ከ3 ሚሊዮን 58 ሲህ 640 ማለፉን የሆፕኪንሱ መረጃ ያሳያል።