ሲጠባበቁ የቆዩት መርከቦች በሙሉ በተከፈተው መስመር ለማለፍ አራት ቀን ሊወስድባቸው እንደሚችል ተገልጿል።
አውሮፓን እና እስያን የሚያገናኝ ከሁሉም አጭር የባህር መስመር የሆነውን የስዊዝ ካናል ወይም መተላለፊያ ቦይ ለአንድ ሳምንት ያህል ዘግቶ የቆመው ግዙፍ ዕቃ ጫኝ መርከብ ትናንት መንቀሳቀሱ ተገለጸ። ደቡባዊውን የቦዩን ክፍል አግድመት ዘግቶት የቆየው አራት መቶ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ኤቨር ግሪን የተባለውን መርከብ ቦዩ ዳርና ዳር ያለውን ደለል በመቆፈር እና በጎታች ጀልባዎች በመሳብ ሊንቀሳቀስ ችሏል። መርከቡ ቆሞ በመክረሙ ጉዳት ደርሶበት እንደሆን እንዲሁም ለምን መንቀሳቀስ እንዳልቻለ ምርመራ እየተደረገለት መሆኑም ተገልጿል።
መርከቡ ዘግቶት በቆየው በሲዊዝ ቦዩ በኩል ለማለፍ እየሞከሩ ያሉትን በርካታ መርከቦች ማሳለፉ ቢያንስ አራት ቀን ሊወስድ እንደሚችል የስዊዝ ካናል አስተዳደር ባለሥልጣንና የተባበሩት መንግሥታት የንግድ ልማት ጉባዔ እና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደልፋታህ አል ሲሲ ችግሩ ባይደርስ ጥሩ ነበር፣ ሆኖም በተደረገው ትልቅ ጥረት ሊወገድ ችሏል። የባህር የባህር መተለለፊያ መስመሩን አስፈላጊነት አውስተዋል። ሃገራቸው ከስዊዝ ካናል በዓመት ከአምስት ቢሊዮን እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ ታገኝበታለች።
ኤቨር ግሪን መተላለፊያ መስመሩን በዘጋባቸው ቀናት አንዳንድ የንግድ መርከብ ድርጅቶች መርከቦቻቸው በደቡባዊው የአፍሪካ ጠርዝ በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ዞረው እንዲያቀኑ አድርገው ነበር ።