የኮሮናቫይረስ በዩናይትድ ስቴትስ

  • ቪኦኤ ዜና

ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ

በዩናይትድ ስቴትስ የኮሮናቫይረስ ክትባት ዘመቻ እየቀጠለ ቢሆንም በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር አሁንም ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ የተላላፊ በሽታዎች ተቋሙ ድሬክተር እና የዋይት ሃውስ ከፍተኛ አማካሪው ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ ይህን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት ቃል

ይህ ሊሆን የቻለው ክፍለ ሃገሮች፣ በተለይም በዚህ በተማሪዎች የመጭው ዕረፍት ወቅት አንዳንዶቹን ገደቦች በማንሳታቸው ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት ዕሁድ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል

"የቫይረሱ ስርጭት ከመቀነስ ይልቅ ባለበት ከፍታው ሊቆይ የቻለው፣ ሰው መጠንቀቅ ላይ ችላ በማለቱ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል””

ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያው የአንድ መቶ የአስተዳደራቸው ቀናት ሁለት መቶ ሚሊዮን ክትባት ይሰጣል ብለዋል፤ የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ ሃምሳ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን አሜሪካውይን ቢያንስ የመጀመሪያውን ክትባት ወስደዋል፥ ዘጠና ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ደግሞ ሁለቱንም ወስደው ጨርሰዋል ብሏል።

ይህ በዚህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ ባለፉት ጥቂት ቀናት በየቀኑ ስድሳ ሽህ አዲስ የኮሮናቫይረስ ተያዥ እየተመዘገበ መሆኑን አስታውቃለች። አሳሳቢ መሆኑም ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና በትረምፕ አስተዳደር የዋይት ሃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ የነበሩት ዶ/ር ዴብራ ቢርክስ ትናንት በሰጡት ቃል የክፍለ ሀገራት እና የከተሞች አስተዳደሮች ወረርሽኙ በከፋ ደረጃ ከተዛመተበት ከመጀመሪያው ዙር ተምረው አፈላጊውን የመከላከል እና መቆጣጠር ርምጃ ቢወስዱ ኖሮ በኮቪድ ምክንያት በሃገሪቱ የጠፋው የአምስት መቶ ሃምሳ ሺህ ሰዎች ህይወት እጅግ ይቀንስ ነበር ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ማዕከል መሰረት በዓለም ዙሪያ በቫይረሱ መጠቃቱ የተረጋገጠው ሰው ብዛት ከአንድ መቶ ሃያ ሰባት ሚሊዮን አልፏል።