ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ከእንግዲህ በአንድ ሜትር ብቻ ተራርቀው መቀመጥ ይችላሉ - ሲዲሲ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል /ሲዲሲ/ የትምህርት ቤቶችን የኮቪድ-19 መከላከያ የማህበራዊ ፈቀቅታ መመሪያ አሻሽሏል።

ቀደም ብሎ በነበረው መመሪያ ተማሪዎች በሁለት ሜትር ገደማ ተራርቀው መቀመጥ የነበረባቸው ሲሆን አሁን ግን አፍ እና አፍንጫቸውን በጭንብል እስከተሸፈኑ ድረስ በአንድ ሜትር ርቀት ተቀራርበው መቀመጥ ይችላሉ።

ትምህርት ቤቶች ቀደም ሲል በነበረው ደምብ የትምህርት ክፍል መቀመጫዎችን መውጣት፤ የትምህርት አሰጣጥ ፈረቃውን ማራራቅ እና ሌሎችም የማህበራዊ ርቀት ርምጃዎች መውሰድ የነበረባቸው ሲሆን አዲሱ ደምብ እፎይታ ሰጥቷቸዋል። በአዲሱ መመሪያ መሰረት ተዘግተው የነበሩ ተጨማሪ ትምሀርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ተጨማሪ ተማሪዎች በአካል ተገኝተው እንዲማሩ ዕድል ይሰጣል ተብሏል።

የሲዲሲ የማህበረሰባዊ ርምጃዎች እና የአሳሳቢ የህብረተሰብ ክፍሎች ግብረ ኃይል መሪ ግሬታ ማሴቲ በርቀት በኢንተርኔት አማካይነት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በጉዳዩ ዙሪያ በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶችን መስሪያ ቤታቸው መገምገሙን ገልጸው በዚያ መሰረት ክፍል ውስጥ ጭንብል ማድረግ ቶሎ ቶሎ እጅ መታጠብ እና በክፍሎቹ አየር በትክክል እንዲዘዋወር ከተደረገ መመሪያዎቹን ማሻሻሉ ትክክለኛ ርምጃ እንደሚሆን ከውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል።