"በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚወጡ ሀሰተኛ መረጃዎች ህብረተሰቡን እያሳሳቱ ነው" - የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት አባል እና የስብሰባው ተጋባዥ ተናጋሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ባካሄደውና ህግ የማስከበር ዘመቻ ባለው ርምጃ ዙሪያ በዓለም አቀፍ ተቋማትና በተለያዩ ሚዲያዎች የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ ህብረተሰቡን እያሳሳቱና ውዥምብር ውስጥ እየከተቱ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት የተሰኘ ተቋም አስታወቀ። ጥምረቱ ይህን ያለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚገመግሙ ፅሁፎችን ለተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በድህረ-ገፅ አማካኝነት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

Your browser doesn’t support HTML5

"በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚወጡ ሀሰተኛ መረጃዎች ህብረተሰቡን እያሳሳቱ ነው" - የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት

መቀምጫቸውን በተለያዩ የአለም አገራት ያደረጉ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት ማክሰኞ እለት በዙም አማካኝነት ያካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የማሳወቅና፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎችን የማረም አላማ ያነገበ ነበር።

ከ 200 በላይ ሰዎች ተሳታፊ በሆኑበት ስብሰባ ላይም የአሜሪካ ምክርቤት አባላት፣ የሴኔት የውጪ ጉዳይ ኮሚቴና የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮችና፣ አትላንቲክ ካውንስል እና ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሞክራሲን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ጥናት አጥኚ ድርጅቶች ተገኝተዋል።

አንድ ሰዓት በፈጀው ስብሰባ ላይም በህወሀት ታሪክ ላይ ተመስርቶ አሁን በህወሀትና በፌደራል መንግስቱ መሀከል የተከሰተውን ችግር የሚዳስስ፣ ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ የሚያስረዳ፣ በህወሀትና በትግራይ ህዝብ መሀከል የነበረውን ግንኙነት የሚተነትንና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ የተፈጠሩ የተሳሳቱ አመለካከቶችን የሚያሳዩ አጫጭር ገለፃዎች ተደርገዋል።

በሰሜን ካሮላይና ኤ ኤን ቲ ዩንቨርስቲ መምህር የሆኑት የጥምረቱ አባል እና የስብሰባው ተጋባዥ ተናጋሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በትክክል ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲደርስ አለመደረጉና፣ በስፋት የሚወጡ ወገንተኛና የተሳሳቱ መረጃዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ብዥታ ፈጥሯል ይላሉ።

ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የፈጠራቸውን ግንኙነቶች በመጠቀም ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዲደርሱ ያደርግ ነበር የሚሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፣ ይህ መንግስት በጥቅምት ህግ የማስከበር ርምጃ ከመጀመሩ በፊት የተካሄዱ የሰላም አካሄዶች ከግምት ውስጥ እንዳይገቡ አድርጏል ይላሉ።

አድቮኬትስ ፎር ኢትዮጵያ የተሰኘ ሲቪክ ማህበር ወክለው በስበሰባው ላይ ፅሁፋቸውን ያቀረቡትና በአሜሪካን ሀገር የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ የሆኑት ወይዘሮ ሜሮን አሀዱ፣ የተሳሳቱና የተዛቡ ያሏቸው መረጃዎች ሆን ተብለው በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲወጡ እንደሚደረጉ አስረድተዋል። ህወሃት ያቀነባበረው ነው ያሉት ዘመቻ አለም አቀፍ ጋዜጠኞችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ ምክርቤት አባላት ላይ ያነጣጠረ ነበርም ብለዋል። እንደማስረጃም፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በየቀኑ ሀሰተኛ ትርክቶችንና መረጃዎችን የሚያሰራጩ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች እንደሚከፈቱ አሳይተዋል።

"ዋሽንግተን ፖስት ህዳር 8 ላይ ባወጣው ሪፖርት በሚዲያ ላይ የተደረገውን ዘመቻ አሳይቷል። የሪፖርቱ ፀሀፊ "በቅርቡ የወጡ 90 ሺህ ትዊቶችን እና ቃለ መጠይቆች ላይ ምርመራ አድርጌአለሁ። እነዚህ ትዊተሮች ኢንተርኔት በመዘጋቱ ምክንያት በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት የዓለም አቀፉን አመለካከት ለመቃኘት የተከፈቱ ናቸው።" ብላለች። ፀሀፊዋ ከጥቅምት 24 ጀምሮም በቀን የሚከፈቱት የትዊተር አካውንቶች ከ21 ወደ 245 ማደጋቸውንም ጠቅሳለች። እነዚህ ትዊተሮች በከፍተኛ ሁኔታ መንግስትን የሚቃወሙ ናቸው።"

የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ጦርነቱ የገባው ተገዶ መሆኑን የሚያሳይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት፣ በአሜሪካን አገር ካሊፎርኒያ ግዛት ነዋሪ የሆኑትና በግዛቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖችን የሚያስተባብሩት አቶ አንድነት እምሩም፣ ህወሀት የፈጠራ ወሬዎችን ለማሰራጨት ቀድሞ ሲዘጋጅ እንደነበርና በዙም አማካኝነት አስቀድሞ ስልጠናዎችን እንደሰጠ ተናግረዋል።

ሌላው በትግራይ ክልል ተወልደው ያደጉትና በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካን አገር ሜሪላንድ ክፍለጋዛት የሚኖሩት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነጋሲ በየነ ባቀረቡት ፅሁፍ ህወሃትና የትግራይን ህዝብ አንድ አድርጎ ማየት የተሳሳተ መሆኑና ህወሃት ለ30 አመታት የትግራይን ህዝብ ሲጨቁን መኖሩን አስረድተዋል።

"ህወሃት ትግራይን ባስተዳደረበት ያለፉት 30 አመታት የትግራይን ህዝብ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ አልጠቀመውም። ከላይ ያሉት አመራሮች ብቻ ናቸው የስርዓቱ ተጠቃሚ የነበሩት። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው። እንደ አንድ የኮሚዩኒስት ርዕዮተ አለም እንደሚከተል ድርጅት ሁሉንም ኢኮኖሚ ተቆጣጥሮና ህዝቡን የሚቆጣጠርበት መዋቅር አዘጋጅቶ ህዝቡ እርስ በእርሱ እየተጠባበቀ በተለይ ምንም አይነት ተቃዋሚ እንዳይኖር አርጎ ነበር። ይሄ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ከትግራይ ህዝብ አልፎ በሌሎችም ክልሎች ላይ አንዳንዴም ከሀገር ውጪ የሚኖሩ የሚፈፀም ነው።"

በአሜሪካን አገር በትምህርት ዙሪያ በአመራር ስራ ላይ የሚገኙትና በስብሰባው ላይ ጥናት ያቀረቡት ወሰንየለሽ ተስፋ በበኩላቸው፣ በህዋሃት በኩል በተቀናጀ መልኩ ከሚካሄደው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በተጨማሪ መንግስት በቂ መረጃ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ አለማድረሱ ክፍተቱን የበለጠ አስፍቶታል ይላሉ።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማሳወቅና ሆን ተብለው የተፈጠሩ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ለማስተካከል በሚል አላማ በተዘጋጀው ገልፃ ላይ ከተሳታፊዎች ለተንሱ ጥያቀዎች መልስ ተሰጥተዋል። የሀሰት መረጃዎችን በመዋጋት ረገድ መወሰድ ስለሚኖርባቸው ርምጃዎችም ሀሳብ ቀርቧል።

ህወሃትን በተመለከት ለተነሱት ጉዳዮች ምንም አይነት ግንኙነት ባለመኖሩ መልስ ማግኘት ባንችልም፣ ከዚህ በፊት በነበሩት ግዜያት ግን የሚነሱትን ወቀሳዎች ሲያስተባብል መቆየቱ ይታወሳል።