ለትምሕርትና ለሕክምና ህንድ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ኮቪድ- 19 ያሳደረው ጫና

ፎቶ ፋይል ሮይተርስ

በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት በእንቅስቃቄ ላይ ገደብ ከተጣለ በኋላ በትምሕርት እና በሕክምና ምክኒያት ሕንድ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየዕለቱ ተደራራቢ ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ገለፁ። 16 የሚሆኑ ተማሪዎች ፤ ከሙምባይ የሚደረግ ልዩ በረራ እንደሚኖር ሰምተው 36 ሰዓት በመኪና ተጉዘው ሲደርሱ፤ የተባለውን ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

Your browser doesn’t support HTML5

ለትምሕርትና ለሕክምና ህንድ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ኮቪድ- 16 ያሳደረው ጫና

ኒውደሊ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሠራ ቢሆንም እስካሁን ምክኒያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንዳልተሳካለት ተናግረዋል። ጽዮን ግርማ ዘገባ አላት።

ደቡብ ምስራቅ ሕንድ ውስጥ አንድራድ ትራዲሽ ስቴት በሚባል ቦት በትምሕርት ላይ የነበሩ 16 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ኮቪድ -19 ካሳደረባቸው ጫና ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ያደረጉት ትግል እንዳልተሳካላቸውና ሙምባይ ውስጥ ቀጣዩን ሁኔታ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ገለፁ። አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ተማሪ ሁኔታውን እንዳስረዳን ከሆነ፤ ተማሪዎቹ የሚማሩበት ቦታ ከሙምባይ 1ሺሕ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ትምሕርት ቤት ተዘግቷል። በሕንድ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በመጨመሩም ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎባቸዋል።

በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ወስነው፤ “ቴሌግራም” በተሰኘው የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያ አማካኝነት “በህንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ” በሚለው የቡድን ገፅ ላይ ባደረጉት የመረጃ ልውውጥ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ህንድ ለህክምናና ለተለያየ ጉዳይ ሄደው እንቅስቃሴያቸው ለተገደበ ኢትዮጵያዊያን ልዩ አውሮፕላን ማዘጋጀቱን ከአየር መንገዱ ሠራተኛ ይሰማሉ።

ይህም በረራ ትላንት ዕረቡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛል ተብሎ ስለተነገራቸውና በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት የአገር ውስጥ በረራም ስለተቁረጠ በጋራ ባዋጡት ገንገብ 170 ሺሕ ሩፒ( ወደ 2200 የአሜሪካን ዶላር) አካባቢ ከፍለው ከ36 ሰዓታት የአውቶብስ ጉዞ በኋላ ሙምባይ ይደርሳሉ።

ተማሪው ሙምባይ ከደረሱ በኋላ የገጠማቸውን ሁኔታ ሲያስረዱ፤ “በእርግጥ መጀመሪያ ስንነሳ ከአየር መንገዱ ሠራተኛ ጋር እንጂ ከኢምባሲው ጋር አልተነጋገርንም ነበር። ከደረስን በኋላ ግን በረራው አንዴ ተራዝሟል ፤ አንዴ ደግሞ ሂደቱ ገና አልተጠናቀቀም ይለናል። እኛ ደግሞ የከፈልነው የቲኬት ገንዘብ በጣም ውድ ስለነበር በእጃችን ላይ የነበረው ገንዘብ አለቀ። በዚህ ላይ አሁን ያለንበት ቦታ የ”ስጋት ቀጠና” የሚባል ነው። ለጊዜው ሆቴል ውስጥ ገብተናል። ሁላችንም ግን አልከፈልንም።” ይላል።

አብዛኞቹ ተማሪዎች በኢትዮጵያ የዩኒቨርስቲ መምሕር እና በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የተለያየ ቦታ ይሠሩ የነበሩ እንደሆኑ ይኸው ተማሪ ገልፆ፤ መንግሥት ሊያስተምር የላካቸው እንደሆኑ ይናገራል። ከኢምባሲው መፍትሔ ለማግኘት ካደረጉት ከፍተኛ የስልክ ሙከራ በኋላም ዛሬ በሕንድ ኒውደሊ የሚገኙትን አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታን አግኝተው ማነጋገራቸውን ገልፀዋል። አምባሳደሯም፤ ኢምባሲው በትምሕርት እና በሕክምና ምክኒያት ሕንድ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ተግቶ እየሠራ በመሆኑ ትንሽ እንዲታገሱ እንደነገሯቸው ገልፀውልናል። ነገር ግን የተማሪዎቹ ችግር ፋታ የሚሰጥ እንዳልሆን ተማሪው ይናገራል። “እጃችን ላይ ምንም ለሆቴል የምንከፍለው ምንም ዓይነት ገንዘብ የለም። ከሆቴልም መውጣት አንችልም።” ይላል።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ህንድ ሙምባይ ለሕክምና ከሄዱ በኋላ ሕክምናቸውን ቢያጠናቅቁም በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት ወደ አገራቸው መመለስ እንዳልቻሉ ከገለፁልን ኢትዮጵያውያን መካከል እህቱን በማስታመም ላይ የሚገኘው ሚኪያስ ተክለሃይማኖት በኢምባሲው አማካኝነት አስፈላጊውን ሰነድ አሟልተው ጉዞ ለማድረግ አውሮፕላን እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፆልናል።

“እናንተ ካነጋገራቸሁን ከሦስት ቀናት በኋላ ከኢምባሲው ፎርም ተልኮልን ሞተን መልሰን ላክን” ብሎናል። ከዚያም አስፈላጊውን ሰነድ አሟልተው በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ አስረድቶናል። ተማሪዎቹ የጠቀሱት ልዩ አውሮፕላንም የተዘጋጀው ለሁሉም እንደሆነ ገልጾ ነገር ግን አየር መንገዱ በረራውን ለማድረግ ከህንድ መንግሥት በኩል ማግኘት የሚገባውን ሰነድ እየተጠባበቀ እንደሆነ እንደተገለፀላቸው ጠቁሞናል።

በሕንድ ኒውደሊ የሚገኙትን አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታ ዛሬም ሆነ ከዚህ ቀደም መረጃ እንዲሰጡ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ አድርገን በተለያየ ምክኒያት ከእርሳቸው ምላሽ ለማግኘት ሳንችል ቀርተናል።

በሌላ በኩል ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አገባይ አቶ አምሳሉ ትዛዙን ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ጠይቀን፤ መጀመሪያ ላይ የሕክምና ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ 61 ኢትዮጵያውያን እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕንድ መንግሥት እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ

ጋር በመነጋገር 54 ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ነገሮች ከተሳኩም በአንድ ሳምንት ውስጥ እንደሚመልሷቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

በትምሕርት እና በሕክምና ምክኒያት ሕንድ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸ ኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ ያሳደረውን ተፅኖ እንደሚረዱ ገልፀው ነገር ግን ሕንድ ውስጥ መቆየታቸው አንድ ቀን እየጨመረ በሄደ ቁጥር ችግራቸው እየተባባሰ እንደሚሄድ ተናግረዋል።

ህንድ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየተባባሰ በመምጣቱ መጀመሪያ ላይ የተጣለው የሁለት ወራት የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ ያራዘመችው የ15 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቀርቶታል። ኒውደሊና ሙምባይ ኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ከተሰራጨባቸው የህንድ ከተሞች የመጀመሪያው መስመር ላይ ይገኛሉ።

(ለአሜሪካ ድምፅ ጽዮን ግርማ - ከሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ)