በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በወንጂ አካባቢ አምስት ሰዎች ባለፈው ሳምንት በአጋቾች መገደላቸው ቤተሰቦቻቸው ገለፁ


በወንጂ አካባቢ አምስት ሰዎች ባለፈው ሳምንት በአጋቾች መገደላቸው ቤተሰቦቻቸው ገለፁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:01 0:00

ለሳምንት ታግተው ከቆዩ ስድስት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ውስጥ አምስቱ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ተገድለው መገኘታቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች የኾኑ አምስት ሰዎች ለሥራ እንደወጡ ከታገቱ በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ተገድለው መገኘታቸውን፣ የሟች ቤተሰብ አባላት ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በአንድ ተሽከርካሪ ተሳፍረው፣ የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ለሥራ ወደ ፋብሪካው የሸንኮራ ማሳ በማቅናት ላይ ከነበሩ ሠራተኞች መካከል ገቢያቸው ከፍተኛ ነው ተብለው የተገመቱ ስድስቱ መታገታቸውንና ሌሎች መለቀቃቸውን ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የቤተሰብ አባል ጠቁመዋል።

በታጣቂዎች የታገቱት ስድስቱ ሰዎች በነፍስ ወከፍ 600ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ከተጠየቁ በኋላ በድርድር 300ሺሕ ብር እንደተወሰነባቸውም ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

ዳሩ ግን፣ ይኸው ገንዘብ ተሰባስቦ ለአጋቾቹ ለመስጠት በሒደት ላይ እያለ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ክፍያው እንዳይፈጸም በማከላከሉ፣ ከስድስቱ መካከል አምስቱ ተገድለዋል፤ ሲሉ ለደኅንነታቸው በመስጋት ማንነታቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪዎች አስረድተዋል፡፡ አንዱ ደግሞ የደረሰበት እንደማይታወቅ ጠቁመዋል።

ሌላው በተመሳሳይ ምክኒያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቤተሰብ አባል ፣ የታጋች ቤተሰብ አባላትን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የተሰበሰበውን የማስለቀቂያ ገንዘብ ለአጋቾቹ ለመክፈል ሲዘጋጁ በፖሊስ መያዛቸውን ተናግረዋል። የሟቾቹ አስክሬን ሲገኝ ግድያው አሠቃቂ እንደነበረም አክለው ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳስረዱት፣ ግድያው የተፈጸመባቸው አምስቱም የፋብሪካው ሠራተኞች ወንዶች ሲኾኑ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪም ነበሩ፡፡ ከሟቾቹ አራቱ፣ ፋብሪካውን ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ አንጋፋ ሠራተኞች ሲኾኑ፣ ሌላውም ወጣት ሠራተኛ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አካባቢው ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበት እንደኾነ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የደኅንነት ስጋት መኖሩን አክለው አመልክተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተያየት ለማግኘት፣ የዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋራ ስልክ ደውለን ቆይተን እንድንደውል ከነገሩን በኋላ ስልካቸውን ባለማንሣታቸው፣ የዞኑ አስተዳዳሪ የእጅ ስልክ ደግሞ ጥሪ ባለመቀበሉ፣ ሙከራችን አልተሳካም፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በሰላማውያን ሰዎች ላይ በየጊዜው እገታ እና ግድያ ከሚፈጸምባቸው ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡

በዞኑ፣ ቅርብ ጊዜ ከተፈጸሙ እገታዎች እና ግድያዎች መካከል፣ ባለፈው ወር የካቲት 11 ቀን፣ በዝቋላ አምስት ገዳማውያን አባቶች ከታገቱ በኋላ አራቱ መገደላቸው ይታወሳል፡፡ በመተሃራ ከተማ አካባቢም፣ ታኅሣሥ 19 ቀን በተፈጸመ ጥቃት፣ በአንድ ተሸከርካሪ ውስጥ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ፣ 10 ሰዎች ደግሞ ለቀናት ከታገቱ በኋላ መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በጉዳዩ ላይ ከፌደራል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ተጨማሪ መረጃን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG