በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ለሽብርተኝነት መፍትሄ እያፈላለጉ ነው


የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ለሽብርተኝነት መፍትሄ እያፈላለጉ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:58 0:00

የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች በቀጠናቸው የተስፋፋውን ሽብርተኝነትና በተባባሰው የደህንነት ችግር ላይ ለመነጋገር ትናንት ማክሰኞ በአክራ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡

ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ አይቮሪ ኮስት እና ቶጎን የሚያካትተው የአፍሪካ ተነሳሽነት አባላት የተነጋገሩት፣ ከሰሃል ተነስቶ ወደ አካባቢያቸው የተዛመተውን ሽብርተኝነት ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው፡፡

የሩሲያ ተጽዕኖ እየጠነከረ ሲመጣ፣ አውሮፓውያን ኃይሎች አካባቢውን ለቀው እየወጡ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የአክራ ተነሳሽነት፣ ሰባት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች፣ በቡርኪና ፋሶና ኒጀር በኩል በሰሜኑ የድንበሮቻቸው አቅጣጫ እየጨመረ የመጣውን እስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት፣ በጋራ ለመከላከል የፈጠሩት፣ የደህንነት ማስጠበቂያ ትስስር ነው፡፡

ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ የመጀመሪያው በሆነው የአክራ ተነሳሽነት ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ እየጨመረ የመጣውን ሽብርተኝነት በጋራ ለመዋጋት ለአባል አገራት ተባባሮ መስራቱ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

“ምዕራብ አፍሪካ በአሸባሪነት እና በአመጽ ጽንፈኝነት እየተሰቃየች መሆኑ እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ሽብርተኝነት በአካባቢው በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። ዛሬ፣ በአካባቢው ስኬት በሚመስለው ድሎቻቸው የተደፋፈሩት የአሸባሪ ቡድኖች፣ አዳዲስ የሽብር እንቅስቃሴዎችን የሚያራምዱባቸውን አካባቢዎች እየፈለጉ ነው፡፡ ይህ ስኬታቸው ሽብርን ከሳህል ወደ ደቡብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እንዲሸጋገር አድርጓል። አክራ ኢኒሼቲቭ የተቋቋመውም ይህን ከሳህል እስከ ባህር ዳርቻ ድረስ ያለውን የሽብርተኝነት ስርጭት ለመግታት ነው።

የጋናው መሪ አባል አገሮቹ የራሳቸው ተነሳሻነት የሚኖራቸው ቢሆንም የውጭ አጋሮቻቸው እንዲረዷቸው ግን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

“የእኛ ግምገማ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ኃላፊነታችን ለመወጣት የምናደርገውን ጥረት የሚያከብሩ ዓለም አቀፍ አጋሮችን በማሳተፍ፣ በራሳችን በኩል የሚፈለግብንን ከፍተኛውን ኃላፊነት ለመሸከም ባለን ቁርጠኝነት ጸንተናል።” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እንደ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ እና ጀርመን የመሳሰሉት ምዕራባውያን አገሮች ሰላም አስከባሪ ኃይሎቻቸውን ከማሊ ያወጡ ሲሆን፣ በምዕራብ አፍሪካ የተበላሸውን የጸጥታ ሁኔታ የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የእንግሊዝ ጦር ኃይሎች ሚኒስትር ጄምስ ሂፒ በበኩላቸው፣ እንግሊዝና ሌሎች የምዕራብ አገሮች ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች ጋር ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነትን በመዋጋት አጋር ሆነው መስራቱን የሚቀጥሉበት ሲሆን፣ ችግሮቻቸውን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው የማይነግሯቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም “የደህንነት ፈተና መኖሩን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ የብሪታኒያ ታጣቂ ሃይሎች በአክራ ኢኒሼቲቭ ውስጥ ካሉት ከብዙዎቹ ሀገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላላቸው እሱንም ለመጠቀም ዝግጁ ነን። ይህ በምዕራብ አፍሪካ ያለ የአካባቢው ችግር በመሆኑ መፍትሄ ለመስጠት መፈለግዎ ትክክል ነው። ነገር ግን እዚህ ያለው አለመረጋጋት እና የደህንነት ችግር በኛ በአውሮፓም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስላሳደረ እኛም በምንችለው መንገድ እርስዎን ለመርዳት ዝግጁ መሆናችን ተገቢ ነው።” ብለዋል፡፡

በአክራ የደህንነት ፖሊስ ምርምር ተቋም የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በደህንነት ጉዳዮች የተካኑት አዳም ቦና ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት መሪዎቹ ተራዎቹን ዜጎች እስካላሳተፉ ድረስ በምዕራብ አፍሪካ የሚደረገው የጸረ ሽብር እንቅስቃሴ ምንም ትርጉም አይኖረውም” ይላሉ፡፡

ዝም ብለን ተነስተን ልንጨርሰው አንችልም፡፡ ትክክለኛ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው።” ያሉት አዳም “በመሪዎቹ በኩል ፍቃደኝነት ሊኖር ይገባል፣ ነገር ግን ዜጎች አንድ ነገር ሲያደርጉ፣ አስፈጻሚዎች ደግሞ ሌላ ነገር ሲያደርጉ ከፍተኛ የግንኙነት ክፍተት ተፈጥሯል። ያለ ህዝብ ተሳትፎ ሽብርተኝነትን መዋጋት አትችልም… እና እነሱ የሚያደርጉትም ያንን አይደለም።” ሲሉ ዜጎችን ማሳተፍ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG