በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ፕሬዚዳንቷን እንድትለይ የውጭ ፖሊሲ ቁልፍ ጉዳይ ነው


አገረ ገዥ ሚት ራምኒ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባ እና አከራካሪው አንጋፋው የሲቢኤስ ኒውስ ጋዜጠኛ ባብ ሺፈር
አገረ ገዥ ሚት ራምኒ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባ እና አከራካሪው አንጋፋው የሲቢኤስ ኒውስ ጋዜጠኛ ባብ ሺፈር

የመጨረሻው “እሰጣገባ” ተካሄደ፡፡


please wait

No media source currently available

0:00 0:09:12 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ


please wait

No media source currently available

0:00 2:00:00 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ


ለዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ ምርጫ ሁለት ሣምንታት ሲቀሩት የተካሄደው የመጨረሻው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ክርክር “የትኛው ዕጩ ለአሜሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚነትና የጦር ኃይሎቿ ጠቅላይ አዛዥነት የተሻለ ብቃት አለው?” ለሚለው ጥያቄ አሜሪካዊያን ለራሣቸው መልስ እንዲሠጡ፤ ድምፃቸውንም የት እንደሚጥሉ እንዲወስኑ ምናልባት የመጨረሻው አጋጣሚ ነው ተብሎ በብዙዎች ታምኗል፡፡

በፍሎሪዳው የቦካ ሬተን ሊን ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የአገረ ገዥ ሚት ራምኒ የእሰጥ አገባ ግጥሚያ የተከፈተው ከዘውድና ከአንበሣ አንዱን ጠርተው፤ ሣንቲም ወደላይ ተወርውራ ስታርፍ በወደቀችላቸው ሚት ራምኒ የመጀመሪያ መላሽነትና ተናጋሪነት ነበር፡፡

እናም ታዲያ ሃገረ ገዥው ንግግራቸውን የጀመሩት ባራክ ኦባማ በእሥላማዊ አክራሪዎች ላይ የከፈቱትን ጥቃት በመንቀፍ ነበር፡፡ “ከዚህ ውጥንቅጥ ለመውጣት መደዳውን ገድለን አንችለውም’ኮ” አሉ፡፡

ሚስተር ኦባማም ተቀብለው “ሚስተር ራምኒ በሁሉም የውጭ ፖሊሲ ምርጫዎቻቸው ላይ የተሣሣቱ ናቸው” አሏቸው፡፡

“ሚስተር ፕሬዚዳንት - አሉ ራምኒ ደግሞ በተራቸው - እኔን መውቀስ እኮ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁከት ለማስቆም አጀንዳ ሊሆን አይችልም፡፡” ደግሞም ኦባማ በዚያ አካባቢ የተከተሉት ፖሊሲ አሜሪካ የነበራት ተስፋ “ሙሉ በሙሉ የተቀለበሰበት አካሄድ ነው” አሉ፡፡



“ኦሣሚ ቢን ላደንን በማስወገዳቸውና በአል-ቃይዳ አመራር ላይ በመዝመታቸው አድናቆቴን ልገልፅላቸው አወድዳለሁ - አሉ አገረ ገዥ ራምኒ - ከዚህ ውጥንቅጥ ግን መደዳውን እየገደልን መቀጠል አንችልም፡፡ ይህንን ገና ማፈግፈግ ያልጀመረ፣ ያልተደበቀም ሥር-ነቀልና አክራሪ ፅንፈኝነት የእሥልምናው ዓለም እና ሌላውም የዓለም ክፍል እንዲያወግዘው የሚያግዘውን አጠቃላይና ብቃት ያለው ሥልት ማውጣትና ወደ ሥራ ማስገባት ይጠበቅብናል፡፡”

ሚስተር ኦባማም በአካባቢው ሠላምና ዴሞክራሲ እንዲሠፍን አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር መሥራቷን ገልፀው ሊብያን እንደምሣሌ አንስተዋል፡፡
“ወታደሮቻችንን ሣናሰማራ፣ ከኢራቅ የሁለት ሣምንት ወጭያችን ባነሰ ወጭ ለአርባ ዓመታት በአምባገነናዊ ቀንበር ሥር የነበረችን ሃገር፣ አሜሪካዊያንን ከገደለ ጨቋኝ ነፃ አውጥተናል፡፡ ደግሞም ምንም እንኳ ይህ አሣዛኝ ታሪክ ቢፈጠርም በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ ሊብያዊያን ቤንጋዚ አደባባይ ላይ ወጥተው ‘አሜሪካ ወዳጃችን ነች፤ ከእርሷ ጋር እንቆማለን’ ሲሉ ታይተዋል፡፡” ብለዋል ፕሬዚዳንት ኦባማ፡፡

ኢራንን በተመለከተ እስከአሁን ታይተው የማይታወቁ እጅግ የከበዱ ማዕቀቦችን በመጣል አስተዳደራቸው “ጥንካሬ”ውን ማሣየቱን ሚስተር ኦባማ አስረድተዋል፡፡

ሚስተር ራምኒም “ዓለም ባለኒኩሊየር ኢራንን ለማየት በአራት ዓመታት ተጠግቷል” ብለዋል፡፡ በመቀጠልም “ኢራናዊያንም አሜሪካዊ ጥንካሬን እንጋፈጣለን ብለው ሲያስቡ ያጋጠማቸው ግን ደካማነት ነው፡፡” አሉ፡፡

ለዩናይትድ ስቴትስ ትልቁ ሥጋቷ ምንድነው ብለው እንደሚያስቡ ራምኒ ሲጠየቁ “የኢራን የኒኩሌር ፕሮግራም” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ሚስተር ኦባማ ደግሞ “የሽብር መረቦች ናቸው - አሉና - በንቃት መቀጠል ይገባናል” ሲሉም አከሉ፡፡

ሚስተር ራምኒ የኦባማን ወታደራዊ በጀት “ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው ሲሉ” አጣጥለውታል፡፡ “የአሜሪካ የአየር ኃይል ከተመሠረተበት እአአ ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ ባልነበረ ሁኔታ ያነሠ፤ የባሕር ኃይሏም ከ1917 ዓ.ም ጀምሮ ካለው ጊዜ ሁሉ እጅግ ያነሠ ሆኗል” ብለዋል፡፡

“ይህ በእኔ አስተያየት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እጅግ የገዘፈው ኃላፊነቱ የአሜሪካን ሕዝብ ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ እኔ ብሆን ወታደራዊ በጀታችንን በአንድ ትሪልዮን ዶላር አልቆርጥም፡፡ ይህ ፕሬዚዳንቱ የቆረጧቸው የበጀት ቅምሮች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን መረጋጋት የሌለውና ለአደጋ የተጋለጠ የሚያደርገው ይመስለኛል” ብለዋል አገረ ገዥ ራምኒ፡፡

ሚስተር ኦባማ በሰጡት ምላሽ ግን ወታደራዊውን በጀት እንደማይቆርጡ ተናግረዋል፡፡ “የሆነው - አሉ ኦባማ ጦሩ የያዘው የነበረውን በጀት ነው፡፡” ይልቅ ተቀናቃኛቸው የሚከተሉት ያረጁና ያፈጁ ፖሊሲዎችን መሆኑን በመግለፅ ወቅሰዋቸዋል፡፡
“የባሕር ኃይሉን አንስተዋል፤ ለምሣሌ፡፡ አሁን ያለን የመርከቦች ቁጥር በ1916 ዓ.ም ከነበሩን ያነሰ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አዩ፤ አገረ ገዥ ሆይ! የፈረሶቻችንና የጎራዴዎቻችንም ቁጥር እንዲሁ ያነሰ ነው፡፡ ምክንያቱም የሠራዊታችንም ዓይነት ተለውጧልና፡፡” አሉ ኦባማ፡፡

ፓኪስታንን በሚመለከት ኦሣማ ቢን ላደንን ለማግኘት ያለፈቃድ መግባታቸውን “ትክክል ነበር” ሲሉ ኦባማ ተከራክረዋል፡፡ “ቀድመን አስፈቅደን ቢሆን ኖሮ የሽብሩን መሪ አናገኘውም ነበር” አሉ፡፡ “የቢን ላደን መገደል በመስከረም አንዱ የሽብር ጥቃት የሚያፈቅሯቸውን ለተነጠቁ አሜሪካዊያን የመንፈስ ዕረፍትን ሰጥቷል” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ አክለው፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ቢን ላደንን ለማግኘት ወደ ፓኪስታን በመግባቷ ምክንያት ከፓኪስታን ጋር ለተፈጠረው መካረር አስተዳደሩን እንደማይወቅሱ ሚስተር ራምኒ አመልክተው የተሠራው “ትክክለኛ ሥራ ነበር” ብለዋል፡፡ “ይሁን እንጂ አሉ - ሚስተር ራምኒ ዩናይትድ ስቴትስ አንድ መቶ የኒኩሌር አረሮች ካሏት ሃገር አካባቢ መራቅ አትችልም፡፡ በመሆኑም የፓኪስታን ሕዝብ አሁን ካለበት ይልቅ ይበልጥ ኃላፊነት ወደሚሰማው ጎዳና እንዲገባ አብረነው ልንሠራ ይገባናል፡፡”

አፍጋኒስታን የሚገኘውን ጦራቸውን እአአ በ2014 ዓ.ም በማውጣት የጊዜ ሠሌዳ ጉዳይ ላይ ሁለቱም አንድ ዓይነት አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

ሦሪያን በሚመለከት ሁለቱም ተከራካሪዎች ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሣድ መወገድ እንዳለባቸው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ ሚስተር ኦባማ ሲናገሩ አሜሪካ አሁን እያደረገች ያለችው ማድረግ የሚገባትን ተግባር መሆኑንና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተች መሆኗን ገልፀዋል፡፡

​አሜሪካ እየደገፈች ያለችው በሦሪያ መደገፍ ያለባቸው መሆኑን፣ በግብፅ ዴሞክራሲን እየደገፈች መሆኗን፣ በሊብያም ወዳጆቿን እየደገፈች መሆኗን አስዳደራቸው እያረጋገጠ ድጋፉን እየሰጠ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረው በሦሪያ ለወታደራዊ ጥቃት እግራቸውን እንደማያስገቡ፣ ወይም ለተቃዋሚዎቹ ከባድ የጦር መሣሪያ እንደማያጎርፉ አመልክተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ለእሥራኤል በቂ ትኩረት አይሰጡም ሲሉ ራምኒ ቢወቅሱም ኦባማ ግን ክሡን ውድቅ አድርገው “በእሥራኤል ላይ የሚሠነዘር ጥቃት በአሜሪካ ላይ እንደተሠነዘረ ጥቃት ይቆጠራል” ሲሉ ቀደም ብለው አዋጅ ማስነገራቸውን አስታውሰዋል፡፡ እሥራኤልን በአካባቢው “መሠል የሌላት ወዳጅ ናት ሲሉም ጠርተዋታል፡፡

አሜሪካ ከቻይና ጋር ሊኖራት የሚገባውን ግንኙነት አስመልክቶ ሚት ራምኒ “ቻይና የገንዘብ ምንዛሪ አጭበርባሪ ናት ተብላ መፈረጅ ያለባት ሃገር ናት” ብለው እርሣቸው ከተመረጡ በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው ያንን እንደሚያደርጉ ዝተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ያ ተግባር ከቻይና ጋር “የንግድ ጦርነት ውስጥ አይከትተንም ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ አሁን ያለውን የወጭና የገቢ ንግድ ሚዛን አንስተው ሃገራቸው ከዚያ በተሻለ ሁኔታ ውስጥ አለመሆኗን ተናግረዋል፡፡
ባራክ ኦባማ በበኩላቸው አስተዳደራቸው ከቻይና ጋር ባለው ግንኙነት እስከአሁን ታይተው የማይታወቁ የንግድና የምንዛሪ ቁጥጥር እርምጃዎችን መውሰዱንና ጥብቅ ሕግጋትን ማውጣቱን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ሚት ራምኒ እራሣቸው ከሚወነጅሏት ኢራን ጋር ግንኙነት ካላቸው የቻይና ኩባንያዎች ጋር እንደሚናገዱ በመጥቀስ ከስሰዋቸዋል፡፡

በክርክሩ ውስጥ ከሰሜን አፍሪካው የአረብ አብዮት ሁኔታዎች በስተቀር የተነሣ የአፍሪካ አጀንዳ የለም፡፡

በተመዘገቡ ድምፅ ሰጭዎች መካከል በተካሄደ ቅኝት የዴሞክራቲክ ፓርቲው ባራክ ኦባማ በውጭ ፖሊሲ አያያዝ በተፎካካሪያቸው ላይ ለወራት ያህል እጅግ የሰፋ የበላይነት ይዘው ቆይተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተለይ በዚህ ዓመት መስከረም አንድ ቀን በቤንጋዚው የአሜሪካ ቆንስላ ላይ የሽብር ጥቃት ተከፍቶ አምባሣደሯን ጨምሮ አራት አሜሪካዊያን ከተገደሉ ወዲህ ሚስተር ራምኒ በከፈቱባቸው የበረታና የሰላ ዘመቻ የውጭ ጉዳይ አያያዛቸው የሕዝብ ተቀባይነትም ሰሞኑን እየተሸረሸረ ሲመጣ ታይቶ ነበር፡፡

የሚት ራምኒ የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ክህሎት በርግጥ በቀጥታ ከያዙት የባሕር ማዶ ንግዳቸው፣ በውጭ አሜሪካዊ ነዋይ አፍሣሽ ካፒታሊስትነታቸውና ከንግድ ጉዳዮች አደራዳሪነታቸው የረዥም ዘመን ልምዳቸው እምብዛም የዘለለ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ለምርጫው ዕለት አሥራ አራት ቀናት ብቻ ቀርተውት ሣለ በሁለቱ ዕጩዎች መካከል የደጋፊ ልዩነት አለመታየቱ ፉክክሩን እጅግ የጋለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ኤንቢሲ ኒውስ እና ዋል ስትሪት ጁርናል የሚባሉት የዜና ድርጅቶች ሰሞኑን ባካሄዷቸው የመራጭ ቅኝት ፕሬዚዳንት ኦባማ ቀደም ሲል የነበራቸው የሰፋ ልዩነት ጠብቦ አሁን 47 ለ 47 ከመቶ ሆነው መተናነቃቸውን የሚያሣይ ውጤት ይዞ ወጥቷል፡፡
በሰኞው የመጨረሻውና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ በተካሄደው ክርክር በቀጥታ ሲከታተሉ በነበሩና ገና አቋማቸውን ባልለዩ መራጮች ዘንድ በተካሄደ የመጀመሪያ ቀጥተኛ የዳሰሣ ቅኝት ኦባማ የበላይነት ማሣየታቸውን የሚጠቁሙ ቁጥሮች ወጥተዋል፡፡
XS
SM
MD
LG