በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለአፍሪካ ስደተኞች የበለጠ ጥበቃ እንዲደረግ የተመድ ጠየቀ


ለአፍሪካ ስደተኞች የበለጠ ጥበቃ እንዲደረግ የተመድ ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:19 0:00

በአፍሪካ ቀንድ እና ሳህል ከሚገኙ ሃገሮች ወደ ሰሜን አፍሪካ እና አውሮፓ የሚፈልሱ ስደተኞችን ከሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ለመጠበቅ የበለጠ ሥራ እንዲሠራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ጠየቀ። ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በሚጠቀሙት ኢንተርኔት ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዲቻልም መንግሥታት እና የግል ተቋማት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ዩኤንኤችሲ አር አሳስቧል።

ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገሮች ሊደርስባቸው ከሚችል ስቃይ እና ሁከት ሸሽተው ከሀገር የሚወጡ ስደተኞችን እንዲሁም በድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከየሀገራቸው የሚፈልሱ ሰዎችን እንደሚጠቀሙባቸው እና ለሚያሳዝን እንግልት እንደሚዳርጓቸው የድርጅቱ ቃል አቀባይ ሻቢያ ማንቶ ይናገራሉ።

"አንዳንዶቹን በረሃ ውስጥ እንዲሞቱ ትተዋቸው ይሄዳሉ። ሌሎች ተደጋጋሚ ለሆነ የወሲብ እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ገንዘብ ለማግኘ የሚደረግ ጠለፋ፣ የስቃይ ቅጣት እና ሌሎች አካላዊ እና የሥነ-ልቦና ጉዳይ ይዳረጋሉ።” ያሉት ማንቶ “ሰዎችን የማዘዋወር ተግባር እጅግ የተስፋፋ እና በጣም አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ነው።" ብለዋል።

በዩኤንኤችሲአር እና በዳኒሽ የስደተኞች ጉባኤ የድብልቅ ፍልሰተኞች ማዕከል ተዘጋጅቶ ይፋ የተደረገው ሪፖርት ከቡርኪናፋሶ እስከ ካሜሩን፣ ከሶማሊያ እስከ ሱዳን ከሚገኙ 12 ሃገሮች የተሰበሰበ መረጃ ላይ ተመስርቶ የወጣ ነው። ቃል አቀባይዋ ማንቶ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለፁት ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ እና ነጋዴዎች ሥራቸውን ለሚታለሉ የጉዳት ሰለባዎች ለማስተዋወቅ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች

እና የኢንተርኔት ድህረገፆችን ይጠቀማሉ። ኢንተርኔትን፣ ህፃናትን ጨምሮ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ሰዎችን ለመለየት፣ ለማባበል እና ለመመልመል እንደሚጠቀሙባቸውም ይገልፃሉ።

ቃል አቀባይዋ አክለው የሰው አዘዋዋሪዎች በሚጠቀሙት ኢንተርኔት ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዲቻል መንግሥታት እና የግል ተቋማት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ዩኤንኤችሲአር እንደሚያሳስብ ተናግረዋል።

ቃል አቀባይዋ "ተመሳሳይ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ችግሩን ለመግታት ጥቅም ላይ ሊውሉ እና ማኅበረሰቡ ትክክለኛና የሚታመን መረጃ እንዲያገኝ፣ በተሻለ መልኩ ራስችውን እንዲጠብቁ እና በነዚህ ጉዞዎች ሊያጋጥማቸው የሚችሉ አደጋዎችን በግልፅ እንዲያውቁ በማድረግ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ይችላሉ።” ብለዋል።

እነዚህን አደገኛ እና የማያስተማምኑ መንገዶችን ለመጓዝ ለሚመርጡ ደግሞ የጥበቃ አገልግሎቶች እንዲኖሩ ለማድረግ እና የሰዎችን ዝውውር እና የሕገወጥ ንግድን ቀለበት ለማስቆምም እንደሚያገለግሉም ገልፀዋል።

አዲስ የወጣው ሪፖርት ስደተኞች እና ፍልሰተኞች በተለያዩ መንገዶች ሊያገኟቸው ስለሚችሏቸው አገልግሎቶች መረጃ ይሰጣል። በተጨማሪም ከሰዎች ዝውውር እና ፆታዊ ጥቃት ለተረፉ ህፃናት እና ሴቶች ደህንነታቸው የሚጠበቅበት ቦታ እና መጠለያ፣ የህግ አገልግሎት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ሊያገኙ የሚችሉባቸው መንገዶች እንዲፈጠሩ ዩኤንኤችሲአር ጥሪ አቅርቧል።

በተለይ እንደ መዳረሻ የሚቆጠሩ ቁልፍ ቦታዎችን ለይቶ ማወቅ እና ስደተኞች እና ፍልሰተኞች በሳሃራ በረሃ በኩል አቋርጠው መንገድ ለመጀመር ከመወሰናቸው በፊት ስለሚጠብቋቸው አደጋዎች መረጃ የሚያገኙባቸው ቦታዎችን ማቋቋም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የዩኤንኤችሲአር ኃላፊዎች አስረግጠው ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG