በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቴክኖሎጂ ሙያ ራሷን ያወጣች ኢትዮጵያዊት


በቴክኖሎጂ ሙያ ራሷን ያወጣች ኢትዮጵያዊት
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:59 0:00

በቴክኖሎጂ ሙያ ላይ የሚሰማሩ ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ ጋር ሲነፃፀር 26 በመቶ ብቻ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ጥቁር ሴቶች 3 በመቶ ብቻ ናቸው። የዛሬዋ እንግዳችን እሴተ ስዩም ግን እጅግ በጣም ትንሽ ጥቁር ሴቶች በሚገኙበት በዚህ የሙያ ዘርፍ ውስጥ እራሷን አሳድጋ በአለማችን ግዙፍ ከሚባሉት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሀከል፣ ማይክሮሶፍት ካምፓኒ ውስጥ በአመራርነት ታገለግላለች። ባልደረባችን ስመኝሽ የቆየ ከእሴተ ጋር ቆይታ አርጋለች።

እሴተ ስዩም ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደርጃ ትምህርቷን በካቴድራልና በናዝሬት የሴቶች ትምህርት ቤት ተምራ አስረኛ ክፍል ስትደርስ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ያቀናችው እሴተ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ቨርጂንያ በሚገኘው ቲ ሲ ዊሊያምስ ትምህርት ቤት ጨረሰች። በቴክኖሎጂ ሙያ የመሰማራት ህልም ጨርሶ ያልነበራትና በአባቷ ገፋፊነት ህግ ለማጥናት ታስብ የነበረችው እሴተ ለኮሌጅ ኬንታኪ ስቴት ከሄደች በኃላ ያለው የትምህርት ህይወቷ ግን መደበኛ ሂደቱን የተከተለ አልነበረም ትላለች።


በዚህ መልኩ ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቀችው እሴተ የተማረችውንና ልምድ ያካበተችበትን የቢዝነስ አናሊሲስ ትምህርት ከቴክኖሎጂው ጋር አጣምራ እራሷን ለማዘጋጀት ጊዜ አልፈጀባትም። በቴክኖሎጂው ዙሪያ ያሉ አጫጭር ትምህርቶችን በመማርና ለአመታት ከተለያዩ የዳታ መረጃ አሰባሳቢ (ዳታ አናሊቲክስ) ካምፓኒዎች ስትሰራ ቆይታ የዛሬ ሶስት አመት በግዙፉ የቴክኖሎጂ ካምፓኒ፣ ማይክሮሶፍት ውስጥ ተወዳድራ በሲኒየር ከስተመር ሰክሰስ ማናጀርነት (የስኬታማ ደምበኝነት ከፍተኛ ሃላፊ) ሆና ተቀጠረች።


እሴተ በቴክኖሎጂ ሙያ ተቀጥሮ ከመስራት ባለፈ ከጏደኛዋ ጋር በመሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ ድልድይ ሆኖ ለሌሎች እገዛ የሚሰጥ 'ብሪጅ አይቲ ሰፖርት ሰርቪስስ' የተባለ የዳታ ቤዝ ትምህርት ቤት አቇቁመው ላለፉት አምስት አመታት ከመቶ ሃምሳ ተማሪዎች በላይ አስተምረዋል። ከነዚህም ውስጥ 37 የሚሆኑት በተለያዩ የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ተቀጥረው ስኬታማ ሆነዋል ትላለች እሴተ።


በቴክኖሎጂ ሙያዋ ውጤታማ የሆነችው እሴተ በበጎ ስራዎችም ትሳተፋለች። በተለይ አሁን በኮሮና ቫይረስና በኢኮኖሚ መዳከም ምክንያት አሜሪካ ውስጥ ስራቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ ከሁለት ጉዋደኞቿ ጋር በ ሰላሳ ቀን ውስጥ ከ 12 ሺህ ዶላር በላይ አሰባስበው ለመቶ አንድ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ድጋፍ አድርገዋል።


የ20 አመትና የ 8 አመት ወንዶች ልጆች እናት የሆነችው እሴተ የስኬቷ ዋና ሚስጥር በራስ መተማመኔ ነው ትላለች። በተለይ ወጣቶች በትልልቅ ቦታዎች ላይ ተሰሚነት እንዲኖራቸው እራሳቸውን በአግባቡ መግለፅ መቻል አለባቸው ስትልም ልምዷን ታካፍላለች።


በቴክኖሎጂ ላይ ማንም ሰው ጥርጥር ከነበረው ከዚህ ከኮሮና በኃላ ጥቅሙ ጎልቶ ወጥቷል የምትለው እሴተ በመጭው ግዜ እጅግ በጣም ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ የስራ እድሎች ባሉት የቴክኖሎጂ ሙያ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ወጣቶች በሚያገኙት አጋጣሚ እራሳቸውን እያስተማሩና፣ ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ጋር እያዋሃዱ ስኬታማ መሆን ይችላሉ ስትል ትመክራለች ።
XS
SM
MD
LG