በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ፣ ወርኀዊ ደመወዛቸው በወቅቱ እንዲከፈላቸው ጥያቄ በማቅረባቸው ታስረው የቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ዛሬ ከእስር መፈታታቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ።
የታሰሩበትን ጉዳይ ገና ያላወቁ 19 ሰዎች፣ 49 ቀናትን በእስር ካሳለፉ በኋላ፣ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ የተደገፈ ክሥ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ “ነፃ ናችኹ” ተብለው በ50ሺሕ ብር ዋስ መፈታታቸውን ገልጸዋል። ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የሚያገኝባቸው ከኾነ ግን፣ “ክሥ ይመሠረትባችኋል” መባላቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡
ከእስር ስለተፈቱት ሠራተኞች የተጠየቁት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ፣ ጉዳዩ ገና እንዳልተቋጨና በምርመራ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
“በደመወዝ ጥያቄ ሽፋን፣ ሁከት እና ብጥብጥ አሥነስታችኋል፤” በሚል 40 ሠራተኞች ለእስር እንደተዳረጉ፣ ቀደም ሲል የተዘገበ ሲኾን፣ ዛሬ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያሰናበታቸው፣ ሳይለቀቁ በእስር የቆዩ ናቸው።
የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኛ የኾኑት አቶ በረከት ደበበ፣ እርሳቸውን ጨምሮ በአንድ ላይ ታስረው የነበሩ 19 የመንግሥት ሠራተኞች፣ ማስረጃ ስላልተገኘባቸው፣ በዛሬው ዕለት ከእስር መለቀቃቸውን፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
“ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቴ ተነፍጌያለኹ፤” የሚሉት አቶ በረከት፣ በተያዙበት ቀን ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና በድብደባው የተጎዳው የግራ ዐይናቸው እስከ አሁን በደንብ እንደማያይላቸው ገልጸዋል፡፡
ወርኀዊ ደመወዛቸው ወቅቱን ጠብቆ እንዲከፈላቸው ለተከታታይ ወራት ያቀረቡት ማመልከቻ ተቀባይነት ባለማግኘቱ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ አቤቱታቸውን ለብዙኃን መገናኛ በማሰማታቸው፣ በወረዳው መንግሥት ተወንጅለው እንደታሰሩም አስታውሰዋል። ይህም ኹሉ ኾኖ አሁንም፣ የሦስት ወር ደመወዛቸው እንዳልተከፈላቸው፣ አቶ በረከት ተናግረዋል።
“የመንግሥት ሠራተኞችን ለዐመፅ አነሣስተኻል፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቀስቅሰኻል፤” ተብለው መታሰራቸውን የተናገሩት፣ ሌላው የወረዳው ሠራተኛ አቶ አንተነህ ደበበ፣ ጉዳያቸው በሃዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለት ፕሬዚዳንቶች ሲታይ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ይህ ነው የሚባል፣ ሕግንና መደበኛ አሠራርን የተከተለ ክሥ እንዳልተመሠረተባቸው ተናግረዋል።
ከተፈጸመባቸው የመብት ጥሰት በተጨማሪ፣ ሕክምና መከልከላቸውንም የተናገሩት አቶ አንተነህ፣ በእስር ያሳለፏቸው ቀናት፣ “ሕግ ወረቀት ላይ ከመስፈር ውጪ እንደማይከበር ያየኹበት አጋጣሚ ነበር፤” ሲሉም ትዝብታቸውን ገልጸዋል።
የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ሳለ፣ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የሚያቀርብባችኹ ከኾነ ክሡ ይቀጥላል፤ ተብለው መለቀቃቸውን የጠቆሙት አቶ አንተነህ፣ “ተገቢነት የሌለው” ሲሉ ነው አሠራሩን የኮነኑት።
ጉዳዩን አስመልክቶ የአሜሪካ ድምፅ በስልክ የጠየቃቸው፣ የሃዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ሜጫ፣ ታስረው የነበሩ ሠራተኞች የዋስትና መብታቸው ተፈቅዶ መለቀቃቸውን እንደሚያውቁ ገልጸው፣ “ጉዳዩ ግን ገና አልተቋጨም፤ በምርመራ ሒደት ላይ በሚገኝ የፍርድ ቤት ጉዳይ ላይ ማብራርያ መስጠት አልችልም፤” ሲሉ በአጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዛሬ ዕለት ከእስር ከተፈቱት ውጪ፣ በወረዳው አስተዳደር እንደሚፈለጉ የስም ዝርዝራቸው በጽ/ቤቱ ወጥቷል፤ ከተባሉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወረዳውን ለቀው የተሰደዱ መኖራቸውን፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ አስተያየት ሰጪ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
የዞኑ መስተዳድር፣ “ሠራተኞቹን ያሰርናቸው፣ ወርኀዊ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው በመጠየቃቸው ሳይኾን፣ በወንጀል ድርጊት በመሳተፋቸው ነው፤” በሚለው አቋሙ እንደ ጸና ነው።
ብዙ እንግልት ከደረሰባቸውም በኋላ፣ አሁንም የሦስት ወራት ደመወዛቸው እንዳልተከፈላቸው በምሬት የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያው እና ማኅበራዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ጠቅሰው፣ ወርኀዊ ደመወዛቸው በወቅቱ እንዲከፈላቸው ከመጠየቅ በቀር፣ የተሳተፉበት የወንጀል ዐይነት አለመኖሩን በመግለጽ፣ አሁንም መብታቸው ተጠብቆ ለጥያቄያቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።