የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዘዳንት ጄኰብ ዙማ በሳምንቱ ማብቂያ ላይ በሰጡት ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ፥ አገራቸው የዓለሙን የእግር ኳስ ድግስ በአስተማማኝና ባማረ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቋን አስታውቀዋል። እንዲያውም ውድድሩ እንደተጀመረ ቁጠሩት፥ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። የፊታችን ዓርብ ሰኔ ፬ ቀን ፪ ሺህ ፪ ዓ ም ውድድሮቹ ከመጀመራቸው በፊት፥ ፫ ሰዓት የሚወስድ ልዩ ልዩ ትርዒት ይቀርባል ተብሏል።
በዚሁ ታሪካዊ ውድድር የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙት የሀገር መሪዎች ቁጥር ብዛትም ፶ እንደሚደርስ ተነግሯል።
ደቡብ አፍሪቃውያን ተጫዋቾችን፥ እንዲሁም ጐብኚዎችን ለመቀበል ቀዩ ምንጣፍ ዘርግተው አቀባበሉን ለማሳመር በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውንም፥ ጄኰብ ዙማ አብስረዋል።
« ቡድኖቹን፥ ደጋፊዎቻቸውን፥ አገር ጓብኝዎችንና በጠቅላላው የስፖርቱን ቤተሰቦች ወደዚች ውብ አገራችን የምቀበለው በታላቅ አክብሮት ነው። ዓለምን በዚህ ታሪካዊና ከፍተኛ የስፖርት ዝግጅት ላይ የምናስተናግደው በእውነቱ በታላቅ ደስታና ትህትና ነው »
ሚስተር ዙማ አክለውም፥ ደቡብ አፍሪቃውያን ለእግር ኳስ ጨዋታ ያላቸው ፍቅር የቆየና ልባዊ መሆኑን ገልጸው፥ በአገራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ በመብቃታቸው መፈንደቃቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ ለመድረስ አገራቸው ከፍተኛ የፖለቲካ፥ የሶሺያልና የኢኰኖሚ ጐዳና መጓዟንና ሕዝባቸው ለስኬቱ በዋናነት የሚያመሰግነውም አንጋፋውን ብልህ መሪ ኔልሰን ማንዴላን እንደሆነ መስክረዋል።
« በዚህ አጋጣሚ ለብሩህ አመለካከታቸውና ለሰጡት አመራር መሥራቹን ፕሬዘዳንትና ምሳሌአችንን ኔልሰን ሮህሊህላህላ ማንዴላ መሆናቸውን ማረጋገጥና ማመስገን ተገቢ ነው። በርሳቸው ያላሰለሰ ጥረት ነው በዚህች አገር እርቅ የወረደውና ዓለም ታላቁን የዋንጫ ግጥሚያ ደቡብ አፍሪቃ እንድታስተናግድ ሊመርጣት የቻለው። ማንዴላ ለዚህ ታላቅ ዝግጅት እንድንበቃ በግላቸውም ደክመዋል »
የዘጠና ሁለት ዓመት እድሜ ያላቸው ኔልሰን ማንዴላ ዓርብ እለት በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ማቀዳቸውን፥ ገዢው የአፍሪቃ ኰንግሬስ ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ የገለጸ ቢሆንም፥ የልጅ ልጃቸው ግን እርጅናው ስለተጫጫናቸው ምናልባት አይችሉ ይሆናል ብሏል።
ሚስተር ዙማ ግን የመገኘት አለመገኘታቸውን ውሳኔ በመጨረሻ የመስጠቱ ጉዳይ የሚስተር ማንዴላ ይሆናል ብለዋል።
ለማንኛውም ሚስተር ማንዴላ ባለፈው ሐሙስ የደቡብ አፍሪቃን ብሄራዊ ቡድን ባፋና ባፋናን አግኝተው በውድድሩ መልካም እድል እንዲገጥመው ምኞታቸውን የገለጹለት መሆኑ ተዘግቧል።
ማንዴላ አራት ቁጥር የተጻፈበትን የቲሙን አምበል ሹራብ ለብሰው ከስፍራው በደረሱ ጊዜም፥ ተጫዋቾቹ፥ የቤተሰባቸው አባላትና ሠራተኞች በሆታና « አንተን የመሰለ መሪ የለም » እያሉ በዝማሬ ተቀብለዋቸዋል።
ከዚያም የቡድኑ አምበል፥ አሮን ማኰይና ሚስተር ማንዴላን፥ ከተጫዋቾቹ፥ ከዋናው የቲሙ አሰልጣኝ ከካርሎስ አልቤርቶ ፓሬራና ከቡድኑ የቴክኒክና አመራር ባለሥልጣናት ጋር አስተዋውቋል።
ኔልሰን ማንዴላ ልክ ከዛሬ አንድ ወር ካንድ ሳምንት በኋላ ዘጠና ሁለት ዓመታቸውን ያከብራሉ። በመሆኑም የተ መ ድ እለቱን ዓለምአቀፍ የኔልሰን ማንዴላ ቀን ተብሎ እንዲከበር ወስኗል። በዚያን እለትም በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦች፥ ስልሳ ሰባት ደቂቃዎች ጥሩ ሥራ በመሥራት እንዲያሳልፉ ይጠየቃሉ።
ለዚህ የተሰጠው ምክንያትም፥ ማንዴላ ደቡብ አፍሪቃና ዓለምን የተሻለ ሥፍራ እንዲኖራቸው መስዋዕትነት ለከፈሉባቸው ስልሳ ሰባት ዓመታት ክብር ሲባል መሆኑ ታውቋል።
ይህም ብቻ አይደለም የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች በአፍሪቃ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲደረግ የላቀውን ሚና ለተጫወቱት የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዘዳንት ኔልሰን ማንዴላ በጆሃንስበርግ ከተማ ግዙፍ ድልድይ በስማቸው ታንጿል።
፪፻፹፬ ሜትሮች ርዝማኔ ያለው ድልድይ ማዕከላዊውን የንግድ መናኸሪያ ወረዳ ከሰሜኑ ከተማ ጋር ያገናኛል። ይህ በደቡብ አፍሪቃ ትልቁ ነው የሚበለው በማንዴላ ስም የተዘረጋው ድልድይ፥ እንደ ፓሪሱ አይፍል ታወር፥ እንደ ኒውዮርኩ ስታቹ ኦፍ ሊበርቲ፥ ወይም እንደ ሲድኒ ኦስትሬልያው ኦፔራ ሐውስ የሚታይ ነው። በአገር ግንባታው አንፃርም አገሪቱ ለደረሰችበት የምህንድስና ቴክኖሎጂ ዓይነተኛ ምስክር ይሆናል ተብሏል።
ቀደም ሲል ፕሬዘዳንቱ ጄኰብ ዙማ እንደገለጹት ደቡብ አፍሪቃውያን ለእግር ኳስ ስፖርት ከፍተኛ ፍቅር ነው ያላቸው። እግር ኳስ በተፈጥሮው እእደ ወረርሺኝ ከአንዱ ወደ ሌላው በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ በመሆኑ፥ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችና ጐብኚዎች በቆይታቸው ወቅት የሚጋሩት ስሜት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ለደቡብ አፍሪቃውያን የስፖርቱ አፍቃሪዎች እያንዳንዱ ግጥሚያ አላሸነፉበት፥ ድግስ ነው። በዘፈን በጭፈራና በሆታ ነው የሚደመደመው።
ባሁኑ ወቅት የሰላሳ ሁለቱም በዓለም ዋንጫ ፍጻሜው የሚወዳደሩ አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች በየመኪኖች፥ መሥሪያ ቤቶችና የንግድ መደብሮች ሲውለበለቡ ይታያሉ። መንፈሱን ከወዲሁ ከማስፈናቸውም በላይ ጥሩ የገቢ ምንጭ ሆነዋል ላቅራቢዎቹ።
ሳዳም ማአኪ፥ እራሱን የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን ቁጥር አንድ ደጋፊ አድርጐ ነው የሚቆጥረው። ቡድኑ ሲጫወት ያመለጠው አንድም ግጥሚያ እንደለ የሚናገረው ማአኪ፥ ከርስ እስከ እግሩ በቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ያሸበረቁ ልብሶችን ነው የሚለብሰው።
« እግር ኳስ ጨዋታ እወዳለሁ። እኔ ለእግር ኳስ እገዛለሁ። መጠጤም፥ ምግቤም፥ እንቅልፌም እግር ኳስ ነው። ለዚህም ነው የእግር ኳስ ስፖርትን የማፈቅረው »
ትላንት ጆሀንስበርግ ውስጥ ናይጄሪያና ሰሜን ኰሪያ ውድድሮቹ በይፋ ከመጀመራቸው አምስት ቀናት በፊት፥ የመሟሟቂያ ግጥሚያ ባደረጉበት ወቅት ሕዝቡ ገና የስታዲየሙ በሮች ሲከፈቱ ቀድሞ ገብቶ መቀመጫ ለማግኘት ሲጣደፍ በተፈጠረ መጨናነቅ፥ በትንሹ አሥር ሰዎች ተረጋግጠው ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል። ከነዚያም መካከል ዘጠኝ የሚሆኑት በሆስፒታል እርዳታ እንደተደረገላቸው ተዘግቧል።
በድንገቱ ሳቢያም ጨዋታው ለግማሽ ሰዓት ያህል ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ነበር እንደገና የቀጠለው። ናይጄሪያ ሰሜን ኰሪያን ፫ ለ ፩ አሸንፋታለች።
አሁን በደቡብ አፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው አሥራ ዘጠነኛው የዓለም ዋንጫ ውድድር ሊጀመር የቀረው ሦስት ቀናት ከአሥር ሰዓት ገደማ ቢሆን ነው።
በመክፈቻው ዕለት ሁለት ግጥሚያዎች ይደረጋሉ። እነርሱም፥ የ ኤ ምድቦቹ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃና ሜክሲኰ ጆሐንስበርግ ከተማ፥ ዑራጓይና ፈረንሳይ ኬፕታውን ላይ የሚያደርጉት ይሆናል።