በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያና የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁለተኛ ዙር ውይይት ሊያደርጉ ነው


የኢትዮጵያና የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁለተኛ ዙር ውይይት ሊያደርጉ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:45 0:00

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋራ የፈረመችው የባሕር በር አጠቃቀም ስምምነት የፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በሚቀጥለው ሳምንት አንካራ ላይ ተገናኝተው ለሁለተኛ ዙር እንደሚወያዩ የቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ዛሬ ዓርብ አስታወቀዋል።

ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ፣ ወይም በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በመጀመሪያው ቀን፣ ኢትዮጵያ 20 ኪ/ሜ የሚደርስ የባሕር ዳርቻ ከሶማሊላንድ በሊዝ ለመያዝ ስምምነት መፈራረሟ፣ ሶማሊላንድን እንደራሷ ግዛት ከምትቆጥራት ሶማሊያ ጋራ ቅራኔ ውስጥ ከቷታል። ኢትዮጵያ ይህን ችሮታ ለመመለስም ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን ለምታስተዳድረው ሶማሊላንድ ነጻ ሃገር ስለመሆኗ እውቅና ለመስጠት ተስማምታ ነበር ተብሏል።

ሞቃዲሹ ስምምነቱን ሕገ ወጥ ነው በማለት፣ በሃገሪቱ ይገኙ የነበሩትን የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲወጡ አድርጋለች፡፡ በዛች ሃገር ከእስላማዊ አማጺያን ጋራ ለሚደረገው ፍልሚያ እገዛ በማድረግ ላይ ያሉትን የኢትዮጵያ ወታደሮችንም ለማስወጣት ዝታለች፡፡

የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ምኒስትሮች በፊዳን አስተናጋጅነት ባለፈው ወር አንካራ ላይ ለመጀመሪያው ዙር ውይይት ተገናኝተው ነበር።

ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አህመድ ጋራ ተገናኝተው የነበሩት የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን፣ ሁለተኛው ዙር ውይይት በመጪው ሳምንት እንደሚካሄድ ዛሬ ኢስታንቡል ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

ከጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አህመድ ጋራ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ እንደተነጋገሩ የገለጹት ፊዳን፣ “ኢትዮጵያ የሶማሊያን የድንበር እና የፖለቲካ ሉአላዊነት እስካከበረች ድረስ፣ በሶማሊያ በኩል የባሕር በር ተጠቃሚ ትሆናለች፣ ይህም በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት መፍትሄ ይሰጣል” ብለዋል።

ቱርክ የሶማሊያ መንግሥት የቅርብ አጋር ሆናለች። ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ወታደራዊ ሠፈሮችን እና ሌሎችንም መሠረተ ልማቶች ገንብታለች፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊትም ሁለቱ ሃገራት የወታደራዊ እና የኢኮኖሚ ትብብሮችን ተፈራርመዋል።

XS
SM
MD
LG