በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አል-ሻባብ


Kismayo, Somalia
Kismayo, Somalia

አል-ሸባብ የሚሊሻ ቡድን በሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች፣ በኬንያና በአፍሪቃ ሕብረት ኃይሎች ትብብር ድል እየተነሣ ነው።

please wait

No media source currently available

0:00 0:08:28 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ


አል-ሻባብ በቅርቡ ስትራቴጂአዊና የገቢው ምንጭ የነበረችውን ቁልፍ የወደብ ከተማ ኪስማዮን እንዲለቅ መደረጉ አይዘነጋም።
ወታደራዊ ሽንፈት ቢደርስባቸውም ታዲያ የአልሸባብ ከፍተኛ መሪዎች አሁንም አንድነታቸውን እንደጠበቁ መሆናቸውንና ረዘም ያለ ጦርነት ሊኖር እንደሚችልም ዛቻ ያሰማሉ።
አሕመድ ማዶቤ በሚል ስም ለሚታወቁትና ታጣቂ ጀሌዎቻቸው ከኬንያና ከሶማሊያ መንግሥት ኃይሎች ጎን ለተዋጉት ሼክ አህመድ ሞሃመድ ኢስላም የኪስማዮ መውደቅ ጣፋጭ የበቀል ዜና ነው እየተባለ ነው።
ሼህ አህመድ ማዶቤ
ሼህ አህመድ ማዶቤ

ሼክ አህመድ ቀድሞ የአልሸባብ አመራር አባል፤ እንዲያውም ምክትል አዛዡ ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ራስካምቦኒ የሚባለው የሚሊሻ ቡድናቸው ከተቀሩት የአመራር አባላት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር በህዳር 2009 ዓ.ም ከኪስማዮ ተባረረ፤ እርሣቸውም ከአልሻባብ መሪነታቸው በዚያው ተባረሩ።
የኪስማዮ ተወላጅ የሆኑት ማዶቤ ያኔ የነበራቸው አቋምና ያቀረቡትም ሃሣብ ለከተማዋ አስተዳደር የአካባቢውን የጎሣ አባላት ያካተተ ጥምር አስተዳደር እንዲመሠረት የሚጠይቅ ነበር።
“አልሸባብ የፈለገው ግን ሥልጣኑን አሰባስቦና አጠናክሮ አምባገነናዊ ሥርዓት መመሥረት ነበርና የቡድኑ ውድቀት መሠረትም ይኸው የአስተዳደር ዘይቤው ነው” ይላሉ ማዶቤ፡፡ አክለውም እንዲህ አሉ፡- “የመገናኛ ብዙኃን፣ የጂሃድ፣ የደህንነት፣ የአስተዳደር ክፍሎችና ሌሎችም ብዙ አሏቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ የተደረደሩ ስልጣኖች ሁሉ ምንም ኃይል የላቸውም። በሌላ ሰው የሚቀዘፍ ጀልባ ላይ እንደተሣፈሩ የሚቆጠሩ ናቸው። ምንም ጥያቄ ያነሳ ይገደላል። በህዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረተ ድርጅት አይደለም።”
አሕመድ ማዶቤ በአውሮፓው የዘመን አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም በወርኃ ሐምሌ አልሸባብን ከመሠረቱ የድርጅቱ አባቶች አንዱ ናቸው።
ሼህ አህመድ ማዶቤ
ሼህ አህመድ ማዶቤ

በዚያን ጊዜ ሞቃዲሾና አብዛኞቹ ደቡብና ማዕከላዊ ግዛቶች የእስማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በሚባለው ድርጅት ቁጥጥር ሥር ነበሩ። በአልሸባብ ውስጥ አባል የነበሩ የጂሃድ ተከታዮች የእስልምና ፍርድ ቤቶቹ እውነተኛው ጂሃድ ሥራ ላይ እያዋለ አይደልም ሲሉ ይወነጅሉ ነበር። በዚያው በሐምሌ ታዲያ ሃራካት ሙጃሂዲን አል-ሻባብ ወይም የወጣቶች ንቅናቄ ሙጃሃዲን - በአህፅሮት አል-ሸባብ ወይም “ወጣቱ” እየተባለ የሚጠራው ቡድን ተመሠረተ።
አሕመድ ማዶቤም ምክትል ሊቀመንበሩ ሆኑ።
አሁን ያንን ጊዜ ማዶቤ እንዲህ ያስታውሱታል፡- “ለረጅም ጊዜያት ተሰብስበን ከተወያየን በኋላ በጅሃድ ሥርዓት አንድ ለመሆንና አል ሻባብ የሚለውን ስም ለመጠቀም ወሰንን። ፓኪስታን ውስጥ የተማረው ኢስማኢል አራሌ ሊቀመንበር፣ እኔ ደግሞ ከራስካምቦኒ ተወክዬ ምክትሉ እንድሆን ተወሰነ።”
ቡድኑ በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት መሃል ትናንሽ የሙስሊም ኤሚሬቶችን ለመመሥረት በዕቅድ ላይ እንዳለ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሶማሊያን ድንበር ሰብረው ገቡና አሰናከሉት።
በ2006 ዓ.ም ፍጻሜ ላይ አብዛኞች የእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረቱ አባላት ማፈግፈግና መሪዎችም ካገር መሸሽ ጀመሩ። ዩናይትድ ስቴትስ በየካቲት 2007 ዓ.ም በታችኛው ጁባ ክፍለሃገር ባካሄደችው የዓየር ጥቃት አሕመድ ማዶቤ ቆስለው በኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ከሦስት ወራት በኋላ ባለፈው ግንቦት የአልሻባብ መሪ እስማኤል አራሌ ወደ ኤርትራ ለመግባት እየተጓዘ ሳለ ጅቡቲ ውስጥ በአሜሪካው የስለላ ተቋም - ሲአይኤ ተይዞ ወደ ኩባ ደሴቱ የጓንታናሞ ቤይ እሥር ቤት ተወስዷል፡፡
ያኔ አልሻባብ ፈጣን እርምጃ ወስዶ ሁለቱንም ወዲያው ተካቸው፡፡ ሙኽታር አቡ ዙቤር ተብሎ የሚጠራው አሕመድ አብዲ ጎዳኔ በትሩን ተቀብሎ እስከአሁንም የቡድኑ አውራ ሆኖ ይገኛል፡፡
አልሻባብ ብዙውን ጊዜ በመሪው ቀልብ የሚንቀሣቀስ ቡድን ነው ይባላል፡፡ አቡ ዙቤር ፓኪስታን ውስጥ የሠለጠነ የሂሣብ ሥራ ባለሙያ ነው፡፡ ከዚያም በአ.ዘ.አ በ1990ዎቹ ውስጥ ወደ አፍጋኒስታን ድንበር አቋርጦ መግባቱና ምናልባትም የወታደራዊ አዛዥነት ሥልጠና ሣያገኝ እንዳልቀረ ይነገራል፡፡
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ቡድኑ ከተሞችን አንዱን በሌላው ላይ እየጣለ በተከታታይ መቆጣጠር ያዘ፡፡ የጠበቀ ሸሪዓም አወጀባቸው፡፡ ሙዚቃ ማዳመጥ ተከለከለ፡፡ ብዙዎቹ ዓለምአቀፍ የረድዔት ተቋማት ታገዱ፡፡
በተመሣሣይ ሁኔታ በአል ሻባብ ዘንድ የውጭ ኃይሎች ሚና አደገ፡፡ ባለፈው የካቲት ቡድኑ አልቃይዳን መቀላቀሉን በይፋ አሣወቀ፡፡ የአልሻባቡ መሪ አቡ ዙቤይር ይህንን የቡድኑን ውሣኔ ለአልቃይዳው ዋና ለአይማን አል ዛዋሂሪ ባደረሰው መልዕክት ነገረ፡፡
መልዕክቱ እንዲህ ይላል፡-
“ለተከበሩ ኤሚር ሼኽ አይማን አል ዛዋሂሪ፤ አምላክ ይጠብቅዎ፡፡ ይህ መልዕክት የመጣልዎ ከወታደርዎ ከሙኽታር አቡ ዙቤይር ነው፡፡ የተወድዱ ኤሚር ሆይ፤ በአል-ሻባብ አል-ሙጃሂዲን ስም በቅዱስ መፅሐፉ መመሪያና በሃዲስም በተነገረው መሠረት በደግም በክፉም ጊዜያት ለእርስዎ ለመታዘዝና ቃልዎንም ለመፈፀም ግዴታ መግባታችንን እንገልፅልዎታለን፡፡ በሰማዕቱ ኢማማችን በሼኽ ኦሣማ በተደነገገው መሠረት ወደ ጂሃድ እና ወደ መስዋዕት ይምሩን፡፡”
ይህ ውህደት የመጣው ሁለቱም ቡድኖች በእጅጉ በተዳከሙበት ጊዜ በመሆኑ ሁለቱም በሥራቸው ያሉ ጀሌዎቻቸውን መንፈስ ለማነቃቃት ካልረዳቸው በስተቀር እምብዛም ፋይዳ ያለው እርምጃ አይደለም ሲሉ የፖለቲካው ጠበብት ይናገራሉ፡፡
አልሻባብ በሶማሊያ መንግሥትና በአፍሪካ ሕብረት ወታደሮች ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እየደረሰበት ባለው ጥቃት ምክንያት እየተፍረከረከ መሆኑና ባለፈው ዓመት ሶማሊያን አበርትቶ በመታት ድርቅና ቸነፈር ምክንያት ይበልጥ መዳከሙን ብዙዎች ይጠቋቁማሉ፡፡
አሚሶም
አሚሶም

አልሻባብ እየዋል እያደረ የአፍሪካ ሕብረቱን ጥምር ኃይል አሚሶምን በግንባር ውጊያ መግጠም እያቃተው የረባ ፍልሚያም ሳያካሂድ ይዞታዎቹን እየለቀቀና እየሸሸ ሲሆን በተለይ እጅግ ጠንካራ ይዞታውና የሃብትና የኃይል ምንጩም የሆነውን ስትራተጂካዊውን የኪስማዮን ወደብና ከተማውን ድል ተነስቶ መልቀቁ ከሁሉም የጠነከረ ዱላ እንደሆነበት ነው የሚታወቀው፡፡
ወደቡን የንግድ ሸቀጦችን በመቅረጥና ከሰል ወደውጭ ለመላክ ጠገብ ያለ ገንዘብ የሚሰበስብበት ምንጩ እንደነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
አልሻባብ በመሠረቱ አሁንም ቢሆን አብቅቶለታል የሚባል ድርጅት አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የኪስማዮው ሽንፈት ለአልሻባብ በወታደራዊና በይስሙላም ደረጃ ጉዳት ያለው እጦት እንደሆነ ግልፅ ቢሆንም ለተባበሩት ኃይሎች ግን ስትራተጂካዊ ድል አይደለም ይላሉ የፈረንሣዩ ብሔራዊ የሣይንስ ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ባልደረባ ዶ/ር ሮላንድ ማርሻል፡- “የአልሻባብ ስትራተጂ በቅድሚያ አዳዲስ መጠጊያዎችን ማግኘት ነው፡፡ እነዚያ መጠጊያዎቹና መሸሸጊያዎቹ ደግሞ ከዋና ዋና መንገዶች ርቀው የሚገኙ የገጠር አካባቢዎች ናቸው የሚሆኑት፡፡
ሮላንድ ማርሻል - ፈረንሣይ
ሮላንድ ማርሻል - ፈረንሣይ

ከዚያም የሚከተለው ስትራተጂ አሚሶም አሁን የሚቆጣጠረው ሞቃዲሾን ብቻ ሣይሆን እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ከተሞችንም በመሆኑ የሎጂስቲክስ መስመሮቹን ማጥቃት ወይም መቁረጥ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የሎጂስቲክስ ጉዳይ እጅግ አሣሣቢው እየሆነ ነው፡፡ በተመሣሣይ ጊዜም ግለሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች፣ በከተሞች ውስጥ የሚጠመዱ ፈንጂዎችና የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችን የመሣሰሉ ጥቃቶችን በማድረስ ይቀጥላሉ፡፡”
ይህ ስትራተጂው ለአልሻባብ ማዕበሉን ያስወግድለትና ወደ አዲስ ምዕራፍ ይወስደው፤ አልያም የአልሻባብ ዶሴ ይዘጋ ዘንድ ግድ ወደሆነው መጨረሻው ያደርሰው እንደሁ እየኖርን የምናየው ይሆናል - ይላል የተንታኞችና የፖለቲካ አሣቢዎች የዛሬ ድምዳሜ፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡
አሚሶም
አሚሶም

የኬንያ ወታደር በሶማሊያ
የኬንያ ወታደር በሶማሊያ
XS
SM
MD
LG