በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመስጂዶችን መፍረስ ተቃውሞ ወቅት ህይወት መጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ


በመስጂዶችን መፍረስ ተቃውሞ ወቅት ህይወት መጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:37 0:00

አንዋር መስጂድ አካባቢ ዛሬ ከጁምዓ ሶላት በኋላ ተደርጎ የነበረን ተቃውሞ ተከትሎ “መርካቶ አካባቢ ተፈጠረ” ሲል ፖሊስ ከገለፀው ረብሻና ግርግር ጋር ተያይዞ የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱንና በአሥሮች የሚቆጠሩ መጎዳታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ጉዳት ደርሶባቸዋል ከተባሉት መካከል 42 የፖሊስ ባልደረቦችና ረዳቶች እንዲሁም ሌሎች አራት ሰዎች እንደሚገኙባቸው ይኸው የፖሊስ መግለጫ ጠቁሞ “ብጥብጡን መርተዋል፣ አስተባብረዋል ወይም ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ” ሲል የጠረጠራቸውን አሥራ አምስት ሰዎች መያዙን አስታውቋል።

ሁለት የአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አግልግሎት ሰጭ አውቶቡሶች ላይም ጉዳት መድረሱን ይኸው የፖሊስ መግለጫ ይናገራል።

ሁኔታውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ አጭር መግለጫ ‘ጠፋ’ የተባለው ህይወት በማን እንደተፈፀመ አይናገርም።

ሸገር ከተማ ውስጥ የመስጂዶችን መፍረስ በመቃወም አንዋር መስጊድ አካባቢ የነበረውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ሥፍራው ላይ እንደነበረና የሆነውን ሁሉ ማየቱን የተናገረ እማኝ ለቪኦኤ ገልጿል። መስጂዱ ውስጥ የነበሩ ምዕመናንም እንዳይወጡ ለተራዘመ ጊዜ ታግደው እንደነበርም እማኙ ጠቁሟል።

ፒያሳ አካባቢ ባለው ኑር መስጂድም የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደነበር ሌላ እማኝ አመልክቷል።

በአንዋር መስጂድ በነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት የፖሊስ አባላት ወደ መስጂዱ ለመግባት ሙከራ አድርገው እንደነበር ጥቆማዎች ቢደርሱንም ይህንን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ መረጃ ወይም የፖሊስ ቃል ማግኘት አልቻልንም።

በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ 19 መስጂዶች መፍረሳቸውን የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመስጂዶች እና የአውቃፍ ዘርፍ ኃላፊ ሼኽ አብዱልሃኪም ሁሴን በዳሶ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከሁለት ቀናት በፊት ሰጥቶት በነበረ መግለጫ “የከተማ አስተዳደሩ እያካሄደ ነው” ያለውን መስጂዶችን የማፍረስ እንቅስቃሴ አውግዞ ምዕመናኑ ክልሉ ውስጥ በሚገኙ መስጂዶች ሁሉ ዛሬ ግንቦት 18 ተቃውሞ እንዲያሰሙ ጥሪ አስተላልፎ ነበር።

የአሜሪካ ድምፅ ዛሬ ስለነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲሁም መስጂዶችን ማፍረስን በተመለከተ ከሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ከኦሮሚያ ክልል እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ሆኖም የሸገር ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ለቪኦኤ በሰጧቸው መግለጫዎች መስጂዶችን ስለማፍረስ ለይተው ባይናግሩም በከተማው የሚካሄደው ግንባታዎችን የማፍረስ ዘመቻ “ሕግን የማስከበር እርምጃ ነው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የሚፈርሱት ቤቶች አስተዳደሩ እንደሚለው ሕገወጥ ቢሆኑ እንኳ ለነዋሪዎች በቅድሚያ አማራጭ መዘጋጀት እንዳለበት ኢትዮጵያ የፈረመችው ዓለም አቀፍ ሕግ እንደሚደነግግ የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ድርጊቱን በመቃወም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ደግሞ አንድ መቶ ሺህ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG