በዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዘንድ ማለፊያ አጥቶ በእንጥልጥል ሲንከባለል የኖረው የኢነርጂና የአየር ንብረት ለውጥ ሕግን የማስፅደቅ ትግል ዛሬ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይመስላል፡፡ ብዙ ድጋፍ ቢኖረውም ተቃውሞም የበዛበት ይህ ሕግ ዛሬ እንዲነሣ ያደረገው ዩናይትድ ስቴትስን ሰሞኑን የገጠማት ከባድ የተባለ የአካባቢ ብክለት አደጋ ነው፡፡ ኮንግረሱ የራሱን የሕግ ቅጂ ባለፈው ዓመት አሣልፎታል - ሴኔቱን ደጅ እየጠና ነው፡፡
የዘንድሮው የሜክሲኮ ባሕረሰላጤ የተፈጥሮ ጋዝና ድፍድፍ ዘይት ብክለት ዩናይትድ ስቴትስን ለከፋ የአካባቢና የኢኮኖሚ አደጋ አጋልጠዋታል፡፡ አደጋው የመገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የአንጋፋዎቹ ፖለቲከኞችና ተንታኞችም ዕለታዊ አጀንዳ ሆኗል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ላይ ያላት ጥገኝነት ያጫረው የተበረታ ሥጋት ያ የኢነርጂና የአየር ንብረት ሕግ ወደፊት እንዲራመድ ያደርግለታል እየተባለ ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የተፈጥሮ ዘይት ጥገኝነት ቢቀንስ በዓለም ቀዳሚ የተባለችው የአካባቢ በካይ ሃገር ወደአየር የምትለቃቸው ግሪን ሃውስ ጋዞች መጠን ይቀንሣል፤ ዓለማችንም ወደጤናማ አካባቢነት እንድታመራ ጠንካራ መሠረት ያኖርላታል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው ሣምንት ውስጥ በካርኔጊ ሜለን ዩኒቨርሱቲ ተገኝተው ሲናገሩ የሜክሲኮ ባሕረሰላጤውን ድንገተኛ የብክለት አደጋ የሃገራቸውን ንፁህ ኃይል አጠቃቀም እርምጃዎች ለማለፋጠን ወቅታዋና ተጨባጭ ማስረጃና መከራከሪያም አድርገውታል፡፡
ኦባማ ለዩኒቨርሲቲው ታዳሚ ሲናገሩ "መሰል የሌለውን ጥረታችንን ከቤታችንና ከሥራችን ቦታ አንስቶ እስከ አነስተኛና ከባድ ተሽከርካሪዎች ውጤታማ የሆነ የኢነርጂ ተጠቃሚ ማድረግ [አለብን]፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቶቻችንን ደፍነን በሃገራችን የኒኩሌር ኃይል ጎዳና ወደመገስገስ ዕቅዳችን ተሸጋግረን እንገፋለን፣ እናስፋፋለን ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ወደነዳጅ ኩባንያዎች እየገሰገሱ ያሉ የግብር ከፋይ ቢሊዮኖች ዶላሮችን አቁመን ለንፁህ ኢነርጂ ምርምርና መዋዕለነዋይ ቅድሚያ እንሠጣለን ማለት ነው" ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የፒው ማዕከሉ የፖሊሲ ትንታኔ ምክትል ፕሬዚዳንት ስቴፈን ሲደል የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ የሚያወጣው የአየር ንብረት ለውጥ ሕግ የቅድሚያ አጀንዳ እነዚያን አማቂ ጋዞች ለአንዴና ለዘለዓለም ለመዝጋት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን አለበት ሲሉ አሣስበዋል፡፡