በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመተማ ወረዳ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ


በመተማ ወረዳ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:01 0:00

ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ ወደ መተማ ወረዳ በሚወስደው ዋና መንገድ ሲጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪ ላይ ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት፣ አምስት ሰዎች መገደላቸውንና አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን የዐይን እማኞች ነን ያሉ ተናገሩ።

ከጎንደር ከተማ ወደ መተማ ወረዳ ሲያመራ "ነጋዴ ባሕር" ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ወጣ ብሎ ልዩ ስሙ "ኩመር በር" በተባለ ስፍራ፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በታጣቂዎች ጥቃት ጉዳት በደረሰበት ተሽከርካሪ ውስጥ እንደነበር ገልፆ ለደኅንነቱ ስለሚሰጋ ስሙን እንዳንጠቅስ የጠየቀን ወጣት፣ በጥቃቱ እግሩ መመታቱን ተናግሯል።

ስለኹኔታ በስልክ የነገረን እና አኹን በመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል በመታከም ላይ እንደሚገኝ የገለፀልን ይኸው ወጣት፣ በዕለቱ በጎንደር ከተማ ከሚኖሩት እናቱ ጋራ የፋሲካን በዓል አክብሮ ወደ መተማ በመመለስ ላይ እንደነበር ተናግሯል።

በዕለቱ ከጫካ ውስጥ የወጡ ታጣቂዎች፣ በሚያልፉ ተሽከርካሪዎች ላይ በከፈቱት የተኩስ እሩምታ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውንና መኪኖቹም መቆማቸውን ገልጿል።

ታጣቂዎቹም ከቆሙት መኪኖች ውስጥ ተሳፋሪዎችን አስወርደው ወደወጡበት ጫካ ለመውሰድ ሲሞክሩ፣ "አንሔድም" በማለት የተቃወሟቸውን ተኩሰው ሲገድሏቸው መመልከቱን ወጣቱ የዐይን እማኝ አስረድቷል።

ከምዕራብ ጎንደር ዞን ትክል ድንጋይ ቀራንዮ መድኀኔዓለም ከተባለ ገዳም ተነሥተው ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ወደ ቋራ በመጓዝ ላይ እያሉ በተሳፈሩበት ሚኒባስ ታክሲ ላይ የተተኮሰው ጥይት እጃቸውን ማቁሰሉን የነገሩን ሌላዋ የዐይን እማኝ፣ ታጣቂዎቹ እርሳቸው ይጓዙበት የነበረውን ሚኒባስ ታክሲ ጨምሮ ቢያንስ ዐሥር ተሽከርካሪዎችን አስቁመው መመልከታቸውን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎች የታጣዊዎችን ማንነት መለየት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ እና አካባቢው፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና እገታዎች ሲፈጸሙ መቆየቱን በየጊዜው መዘገባችን ይታወሳል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በነበራቸው ቆይታ፣ በአካባቢው ተደጋጋሚ ግድያ እና እገታ እንደሚፈጸም አምነው፣ አካባቢውን የሚያረጋጋ የመንግሥት የጸጥታ ኀይል ስምሪት ተደርጎ እንደነበር ተናግረዋል።

የመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል አስተባባሪ አቶ ሰይፉ አሌ፣ ችግሩ በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም ገልጸው፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለክታሉ።

ያለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥቃት ስለመፈጸሙ መረጃ እንደደረሳቸው የጠቀሱልንና ለጊዜው ስማቸውን በምስጢር እንድንይዝ የጠየቁን አንድ የዞኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በዕለቱ ታጣቂዎቹ 30 ሰዎችንም ከቦታው አግተው እንደወሰዱ አስታውቀዋል።

ኾኖም፣ የጸጥታ ኀይሎች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋራ በመኾን ባደረጉት ርብርብ፣ ታጋቾቹን በማግሥቱ ለማስለቀቅ መቻሉን ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG