በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኬንያ ፓርላማና አዲስ የምርጫ ሕግ


የኬንያ ባንዲራ
የኬንያ ባንዲራ

የኬንያ ፓርላማ የመጭውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሕግ ለማውጣት ክርክር ጀምሯል፡፡ ምርጫው የሚካሄደው በመጭው የአውሮፓዊያን ዓመት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

መጭውን ምርጫ ከአመፅ የፀዳ ማድረግ ነው የኬንያ ፓርላማ ዋነኛ ግብ፡፡ ታዲያ ለእንዲህ ዓይነቱ የምርጫ ሂደት፣ የአመፅ ታሪክም ላለው አካባቢ የሚመጥነው ሕግ ያስፈልገዋል፡፡

ፓርላማው ይህንን ፈተና ይወጣ ዘንድ ነው አሁን የተያያዘውን የረቂቅ ሕግ ክርክር የጀመረው፡፡

ምክር ቤቱ አሁን የደረሰበት አጀንዳ የነፃ ምርጫና የድንበሮች ኮሚሽን ሕግ ነው፡፡ ይህ በአዲሱ ሕገ መንግሥት ውስጥ የሰፈረና የለውጦቹም ማዕዘናት ከሚባሉ ሕግጋት አንዱ ነው የሚሆነው፡፡

በዚህ ሕግ መሠረት የሚቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን ከ1300 በላይ ሰው ለተገደለበት፣ ላለፈው ብጥብጥ መፈጠር ምክንያት የሆኑ ሰበቦችን ሰጥቷል የተባለውን፤ በብልሹነትና ነፃነት በማጣት ብዙ የታማውንና የፈረሰውን ኮሚሽን የሚተካ ይሆናል፡፡

የሕጉ ረቂቅ በፍትሕ ሚኒስትሩ ሙቱላ ኪሎንዞ እና በኬንያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሲሆን ሁሉንም ፓርቲዎች ሊያረካ እንደሚችል ፍንጭ ባሣየ ሁኔታ የተቀናቃኙ ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ፓርቲው ጄምስ ኦሬንጎ ድጋፋቸውን ወዲያው ቸረውታል፡፡

ረቂቁ ከእርሣቸውም አልፎ ከእንደራሴዎቹም ስፋት ያለው ድጋፍ ያገኛል እየተባለ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የምክር ቤቱ አባላት ሕጉ ብርቱ ጥርሶች እንዲኖሩት ይፈልጋሉ፡፡ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር የሚመረጥበት መመዘኛም እጅግ ጠንካራ እንዲሆን የሚሹም አሉ፡፡

ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት እንደራሴ የማርታ ካርዋ ፍላጎት ሕጉን የሚጥስ ሁሉ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው፡፡

በኮሚሽነሮቹ አመራረጥ ላይ በፓርላማው ውስጥ ገና መግባባት የተፈጠረ አይመስልም፡፡ የቀረበው ረቂቅ መራጭና ሃሣብ አቅራቢ ኮሚቴ እንደሚፈጠር የሚጠቁም ቢሆንም አንዳንድ እንደራሴዎች የሚፈልጉት ኮሚሽነሮቹ በፓርቲያቸው እንዲሰየሙ ነው፡፡

ረቂቁ፤ ሕግ ከሆነ በቀረበው ሃሣብ መሠረት ዘጠኝ አባላት የሚኖረው ኮሚቴ ለስድስት ዓመታት በሃገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ምርጫዎችን ሂደቶች ይመራል፤ ያስፈፅማል፡፡

እንደራሴዎቹ አክለው እያቀረቡ ያሉት ሌላው ጥያቄ ፍርድ ቤቶች የምርጫ ውዝግቦችን ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ እንዲያስፈፅሙ ለማስቻል ለውጥ እንዲካሄድባቸው ጭምር ነው፡፡

ኬንያ የረባ የምርጫ ማስፈፀሚያ ሕግ እና አስፈፃማ አካልም እንደሌላት በቅርቡ የወጣ አንድ የነፃ ግምገማ ሪፖርት ወቅሷል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG