የዓለም የጤና ድርጅት መጋቢት 29 የሚውለውን የዘንድሮን የዓለም የጤና ቀን አስቦ የሚውለው ለምግብ ደኅንነት ትኩረት ሰጥቶ ነው፡፡
በምግብ መመረዝ ወይም መበከል ምክንያት የሚፈጠሩ ሕመሞች ዓለምአቀፍ ሥጋት መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም በመላው ዓለሙ የምግብ ምርትና አቅርቦት ሰንሠለት ውስጥ ድንበር ዘለል የሆኑና የተቀናጁ የቁጥጥር አሠራሮች መዘርጋትና መደንገግ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡
በተመረዙ ወይም በተበከሉ ምግቦች ምክንያት ሰዉ ላይ የሚሠፍሩ ከሁለት መቶ በላይ ዓይነት በሽታዎች ሲኖሩ እነዚህም ከተቅማጥ እስከ ካንሠር የሚዘልቁ ናቸው፡፡
በዓለም ዙሪያ በ2010 ዓ.ም (የዛሬ አምስት ዓመት ማለት ነው) ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ሰው በምግብ አመጣሽ በሽታዎችና ሕመሞች የጤና አገልግሎት ማግኘቱንና በዚያው ዓመት ወደ አራት መቶ ሺህ የሚሆን ሰው መሞቱን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
ዕለቱን ኢትዮጵያም “ጤናማ ምግብ ከእርሻ እስከጉርሻ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ እንደሚውል በምግብ፣ መድኃኒትና ጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የምግብ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ለቪኦኤ ገልፀልዋ፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዙት የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ፡፡
"ከእርሻ እስከ ጉርሻ -
የምግብዎን ደኅንነት ይጠብቁ"
የምግብን ደኅንነትና ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ አምስት ቁጥፍ ነጥቦች
- ምግብ ሲያዘጋጁ የራስዎን ንፅሕና ይጠብቁ፤
- የበሰሉ ምግቦችን ካልበሰሉት ጋር አይደባልቁ፣ ወይም አያነካኩ፤
- ምግብዎን በደንብ አብስለው ይመገቡ፤
- ምግብዎን ከመበላሸት መከላከል በሚችል የሙቀት መጠን ያኑሩ፤
- የሚጠቀሙበት ውኃና የምግብ ዝግጅት ግብዓቶች ሁሉ ጤናማና ንፅሕናቸው የተጠበቀ፤ መሆናቸውን፣ የምግቡንም፣ የሚያዘጋጁበትን፣ የሚያበስሉበትና የሚያቀርቡበትን፣ የሚመገቡበትንም ዕቃ ፤ የሚያዘጋጁበትን አካባቢም ፅዳት ይጠብቁ፡፡