በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአይቮሪ ኮስት የተቃዋሚው ታማኞች የፕሬዝዳንት ባግቦን ቤተ-መንግስት ከበቡ


በአይቮሪ ኮስት የንግድ መዲና አቢጆ ተኩሱ ቀጥሏል። የታህሳስ ወሩን የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና የተሰጣቸው ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ ታማኝ ሀይሎች የሎሮን ባግቦን ቤተ-መንግስት ከበዋል።

በአይቮሪኮስት ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለወጡ ነው።

የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ትናንት ማምሻውን ስርጭቱን ማቋረጡን የዋታራ ቃል አቀባይ አሁዋ ዶን ሜሎ ገልጸዋል።

የባግቦ ወታደሮች የአገሪቱን የአየር ማረፊያ ለተባበሩትም መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪዎች አስረክበዋል። የሃገሪቱ ጦር ጠቅላይ አዛዥ በደቡብ አፍሪካው አምባሳደር የመኖሪያ ቤት ተጠግተዋል።

አላሳን ዋታራ የአገሪቱ ጦር አብሯቸው እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

“በጥርጣሬ ላይ ያላቸሁ የጦሩ አባላት፤ ጄኔራሎችም ሆናችሁ መኮንኖችና ተራ ወታደሮች አገራቸሁን የማገልገያ ጊዚያችሁ አሁን መሆኑን አምናችሁ ወደ ህግ ተመለሱ። ጠመንጃ ያነገቡትን ወንድሞቻችሁን የመቀላቀያ ጊዜው አላለፈም” ብለዋል ዋታራ።

አቢጆን ለመቆጣጠር ውጊያው የተፋጠነው ላይቤሪያን በሚያዋስነው የአገሪቱ ክፍል፤ የዋታራ ወታደሮች ያለምንም ቅዋሜ አካባቢውን ነጻ ካወጡ ወዲህ ነው። በዚህ ዘመቻ የፖለቲካ መዲናዋን ያሞሱክሮ እና የሳን ፔድሮ ወደብን ተቆጣጥረዋል።

በስተምስራቅ በኩልም ጋናን በሚያዋስነው ድንበር ድል ቀንቷቸዋል። በአይቮ ሪኮስት ከታህሳሱ ወር የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ወዲህ ከ500 የማያንሱ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ዋና ጸሀፊ ባንጊ ሙን ሁለቱም ተፎካካሪ ጎራዎች ዜጎችን እንዳይጎዱ አስጠንቅቀው፤ ሚስተር ባግቦ ከስልጣን እንዲወርዱና ዋታራ መንግስት እንዲመሰርቱ ጠይቀዋል።

XS
SM
MD
LG