የግድቡን ግንባታ አምርራ ስትቃወም የቆየችው ግብፅም ኢትዮጵያ የግድቡን አንድ የኃይል ማመንጫ ተርባይን ማንቀሳቀሷን በመተቸት መግለጫ አውጥታለች።
ሦስቱ አገሮች በግድቡ ዙሪያ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት ሲደራደሩ ቢቆዩም አንዳች ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።
ግብፅና ሱዳን ግድቡ በሚሞላበት ሁኔታ ላይም ይበጀናል ባሉት መንገድ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ግፊት ማድረጋቸውን የጠቀሰው የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ የተፈለገው ስምምነት ላይ ባይደረስም ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ክረምት ግድቡን መሙላት መጀመሯን አስታውሷል።
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ አቻ የለሽ የሚሆነው ኅዳሴ በሕዝቧ ቁጥር በአህጉሩ ሁለተኛ ትልቅ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ለልማቷ ቁልፍ እንደሆነ ትናገራለች።
በሌላ በኩል ዘጠና ከመቶ የመስኖና የንፁህ ውኃ አቅርቦቷ ምንጭ አባይ የሆነው ግብፅ የኅዳሴ ግድብን ግንባታ የሕልውናዋ አደጋ አድርጋ ታያለች ያለው የኤኤፍፒ ዘገባ ሱዳን በአንፃሩ በያመቱ የሚገጥማትን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ ይቆጣጠራል የሚል ተስፋ ቢኖራትም በሦስቱ ሃገሮች መካከል ስምምነት ካልተደረሰ የራሷ ግድብ ይጎዳል የሚል ስጋት እንዳላት አመልክቷል።
ግብፅ ያሰማችውን ውንጀላ ተንተርሶ የአሜሪካ ድምጽ ለትንታኔ የጋበዛቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መምህሩ የዓለም አቀፍ የውኃ ጉዳዮች አዋቂው ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ “በህዳሴ ግንባታም ሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በተከናወነው ሥራ የተጣሰ ምንም ዓይነት ስምምነት የለም” ይላሉ።