በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጋምቤላ ነፃነት ግንባር አባላት ከእስር እየተለቀቁ ነው


የጋምቤላ ነፃነት ግንባር አባላት ከእስር እየተለቀቁ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:16 0:00

በጋምቤላ ክልል፣ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ጋነግ/ አባላት እና በቡድኑ ስም ታስረው የነበሩ ሰዎች ከእስር እየተለቀቁ መኾኑን ግንባሩ አስታወቀ።

የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ በበኩሉ፣ እስረኞችን መፍታት፥ በሰላም ስምምነቱ ከተገለጹ አንኳር ጉዳዮች አንዱ መኾኑን በመጥቀስ፣ አሁን በእስር ላይ የሚገኙ ቀሪ የቡድኑ አባላትም እንደሚለቀቁ ገልጸዋል።

በክልሉ መንግሥት እና በጋነግ መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት፣ ለክልሉ ሰላም እና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተመልክቷል።

ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ጋነግ/ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል፣ ከክልሉ መንግሥት ጋራ የሰላም ስምምነት ፈርሞ ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሱ የተገለጸው፣ በዚኹ ሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚኹ ጋራ ተያይዞ፣ በቡድኑ ስም ታስረው የነበሩ ሰዎች እና አባላቱም ከእስር ተፈተው ለተሐድሶ ሥልጠና መግባታቸውን፣ የቀድሞው የግንባሩ መሪ ጋትሉዋክ ቡም፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“እስረኞች መፍታት አንዱ ነጥብ ነው። እናም መከናወን የነበረበት የተሐድሶ ሥልጠና ከመጀመሩ በፊት ነበር። ምክንያቱም በእስር ቤት ያሉት አባሎቻችን እና አመራሮቻችን ሥልጠናው ይመለከታቸዋል የሚል አቋም ላይ ስለደረስን ነው።” ያሉት አቶ ጋትሉዋክ ወደ 14 የሚሆኑ አባሎቻቸው መለየታቸውን እና ከእነዚያ ውስጥ ከእስር የተለቀቁት አምስት ብቻ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ይኹንና፣ አሁንም ያልተለቀቁ ቀሪ አባሎቻቸውና ሌሎችም ሰዎች መኖራቸውን ጋትሉዋክ ቡም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት በበኩላቸው፣ እስረኞችን መፍታት፣ የሰላም ስምምነቱ አንድ አካል መኾኑን ተቀብለው፣ የተፈቱ እንዳሉ ሁሉ፣ በጋነግ ምክንያት ታስረው ሳይፈቱ የቀሩም ግለሰቦች፣ በስምምነቱ መሠረት እንደሚፈቱ አመልክተዋል።

“በእነርሱ ስም የታሰሩ 18 ስምንት ሰዎች ናቸው። ነገር ግን ወደ ሰባት የሚኾኑት የወጡ ሲሆን አምስት የሚኾኑት ደግሞ ለመውጣት በሂደት ላይ ናቸው” ብለዋል። በአጠቃላይ 12 ሰዎች ይወጣሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል። “ሌሎች ጉዳያቸው በፌደራል መንግሥቱ የተያዘ ሲሆን በፍትህ ቢሮ በኩል ይፈጸማል። ሌላ ወንጀል ከሌላቸው በስተቀር በስምምነቱ መሰረት ይፈታሉ።” ብለዋል።

ከዚህ በኋላ ለሚመጡ የጋነግ አባላት ጭምር፣ የተሐድሶ ሥልጠና ለመስጠት፣ የክልሉ መንግሥት ዝግጁ መኾኑን የጠቆሙት አቶ ኡቶው፣ “ክልሉን ከጸጥታ ስጋት ነጻ ያደርገዋል። ዜጎች ያለ ስጋት መንቀሳቀስ ይችላሉ። ተበላሽተው የነበሩ የማኅበራዊ ትስስሮችን መልሶ ወደ ሰላም የሚመለሱበት ሁኔታ፤ ጥርጣሬዎች ነበሩ። ስለዚህ እነዚህን ጥርጣሬዎች የማስወገድና በይቅርታና በሰላም ሰዎች አንድ ላይ እንዲኖሩ ማድረግ ነው።” የተደረገው የሰላም ስምምነት ያመጣል ስላሉት ፋይዳም አብራርተዋል።

የቀድሞው ጦር መሪ ጋትሉዋክ ቡም፣ ድርጅታቸው ጋነግ፥ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋራ ግንኙነቱን በማቆም ታጣቂው ኃይል ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጣ ጥሪ ስለ ማቅረባቸው መዘገባችን ይታወሳል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በኾነችው የዛንዚባር ደሴት፣ አደራዳሪ ወገኖች እና ዓለም አቀፍ አካላት በተገኙበት፣ ላለፉት ሰባት ቀናት በቅድመ ድርድር ንግግር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

XS
SM
MD
LG