በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀድሞ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ም/ዋና ዳይሬክተር ዛሬ ከእስር ተለቀቁ


የቀድሞ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ም/ዋና ዳይሬክተር ዛሬ ከእስር ተለቀቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:16 0:00

በአቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ስር ጉዳያቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲታይ የነበሩ ዘጠኝ ተከሳሾች በዛሬው ዕለት ከእስር ተለቀቁ፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁን እና በደህንነት ተቋሙ ውስጥ የሥራ ሐላፊ የነበሩት አቶ አማኑኤል ኪሮስን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾች በዛሬው ዕለት ከእስር መፈታታቸውን የአሜሪካ ድምፅ ከቤተሰቦቻቸው አረጋግጧል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ባለፈው ሐሙስ ዕለት ዘጠኙ ተከሳሾች ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ከአራት ወር እስር እንዲቀጡ ወስኖባቸው ነበር፡፡ ከዘጠኙ ተከሳሾች ሦስቱ የእስር ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው በእለቱ እንዲፈቱ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ የደህንነት ተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ ሰባቱ ተከሳሾችም ከተያዙበት ከጥቅምት 30 ቀን 2011 ጀምሮ ከአራት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ታስረው በመቆየታቸው፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ በአመክሮ እንደሚፈቱ ከጠበቆቻቸው አንዱ አቶ ክፍላይ መሓሪ ሐሙስ ዕለት ለአሜሪካ ድምፅ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታኅሣስ 7/2015 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በሰጠበት ጊዜ፣ አቶ መዓሾ ኪዳነ እና አቶ ተሾመ ሀይሌ የተባሉ ሁለት ተከሳሾች ከአራት ዓመት ክርክር በኋላ በነፃ መለቀቃቸውንም መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በዛሬው ዕለት ከእስር የተፈቱት ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ጉዳያቸው ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር እንደሚያያዝ በመገለፁ፤ የመነሻ ክሳቸው ተቀይሮ በወንጀል ሕግ እንዲከላከሉ መደረጉን የህግ አማካሪው አቶ ክፍላይ መሐሪ ጠቅሰዋል፡፡የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ከአምስት ወራት በፊት ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ በነበሩት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳሪክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ፣ በእስር ላይ ሆነው ሲከራከሩ በቆዩትና የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችሉ በገለፁ ተከሳሾች ላይ ከ 18 አመት እስከ ዘጠኝ ወር የእስር የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG