በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ፖለቲካና የዘንድሮ ተማሪዎች


በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ተማሪዎች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በዛሬ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላቸው ተሣትፎ ምን ይመስላል?

please wait

No media source currently available

0:00 0:05:26 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ተማሪዎች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በዛሬ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላቸው ተሣትፎ ምን ይመስላል?

በመንግሥቱ አመራር ላይ ያለው ኢሕአዴግ ምርጫውን ማሸነፉ ከተነገረ እነሆ አንድ ሁለት ሣምንታት ፈቀቅ አሉ፡፡

ይህ ገዥ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ አይደለም እየተባለ ሲከሰስ ብዙ ጊዜ ይሰማል፡፡ ለወትሮ፤ በቀደሙ ዓመታት፤ አምባገነን የሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥታት ከተማሪዎች የሚያጋጥማቸው ፈተና እንዲህ ቀላል አልነበረም፡፡ የሃገሪቱ ታሪክ ብዙ የተማሪ አመፅ፣ ብዙ ሁከት፣ ብዙ ጥያቄና ንቅናቄን መዝግቦ ይዟል፡፡

ዛሬ ግን የተማሪው በፖለቲካው ውስጥ የመሣተፉ ቆሌ እምብዛም የተነቃቃ አይደለም እየተባለ ነው፡፡ ተማሪው የፖለቲካ ነገር-ዓለሙን ችላ ያለው ይመስላል፡፡

ናትናኤልም በዚህ ይስማማል፡፡ ናትናኤል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪ ነው፡፡ ስለድሮዎቹ ያለውን ክብር ይናገራል፡፡

“ለከፈሉት መስዋዕትነት አድናቆት አለኝ፡፡ የእኔ ዘመነኛ ወጣቶችና ተማሪዎች እንደዚያ የማይነቃነቁት ምናልባት የምንሮጥለት አንድ ነጥብ ስላሌለን ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ወጣቱ ተከፋፍሏል፡፡ ምናልባት በጎሣ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም በሃብታሙና በድኃው መካከል በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት የአቅምም ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን አድርገው ለአንድ ዓላማ መቆም አልቻሉም፡፡” ብሏል፡፡

ከመለያየቱ በተጨማሪ ደግሞ ሃሣቡን በነፃነት የመተንፈስ ችግር እንዳለበት ብዙው ተማሪ ይናገራል፡፡ ስለፖለቲካ የሚነጋገሩት ከቅርብ ጓደኞቻቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሆኑ ጊዜ ደኅንነትና የመናገር ምቾት ሲሰማቸው ነው፡፡ ናትናኤልም ሙሉ ማንነቱን መናገር አልፈለገም፡፡ የተለየ ሃሣብ መያዝ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ብሎ ያስባል፡፡ “ሙሉ በሙሉ ዴሞክራሲያዊት በሆነች ሃገር ውስጥ ሃሣብን መግለፅና በዚህች ሃገር ውስጥ ሆነህ ሃሣብን መግለፅ አንድ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል አይመስለኝም፡፡” ብሏል፡፡

ዛሬ እንዲህ ለዘብተኛ ለመሆኑ ተማሪው መውቀስ ያለበት እራሱን ነው - ይላል የሥነ-ምጣኔኃብት ተማሪው ምኒልክ፡፡ ወጣቱ እኮ ዛሬ የተሻለ መረጃ የማግኘት የተሻለ ዕድል አለው - እንደምኒልክ፡፡ መከፋፈሉ ተማሪው በተሣካ ሁኔታ እንዳይደራጅ እናዳደረገው ይናገራል፡፡

“እኛ እንደቀደሙት ልንሞትለት የሚገባን ጉዳይ ካለ፤ የቀድሞዎቹ የሚሞቱለት ጉዳይ ነበር፡፡ እነርሱ ቢወድቁ የፋናቸውን ቀንዲል አንስቶ እስከ ፍፃሜው መስመር የሚያደርስ እንዳለ ያስቡ ነበር፡፡ ስለዚያ ጨርሶ አይጠራጠሩም ነበር፡፡ እኛ ጋ አንድነት የለም፡፡ እኔ ከሞትኩ፤ በቃ! ሞትኩ ነው፡፡ የቅርብ ጓደኞቼ ቀብሬ ላይ ይገኛሉ፤ ቤተሰቤ፤ በቃ! ታሪኩ ተፈፀመ፡፡” ብሏል፡፡

የበፊቱ ሰውዬ፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም በተለይ ለተማሪዎች ጥሩ አልነበሩም፡፡ ክፉ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ሃገራቸውን እየጣሉ በየአቅጣጫው እንዲያመልጡ፤ እንዲነጉዱ አድርገዋል፡፡ ብዙዎች ብረት እያነሡ የትጥቅ ትግል ውስጥ እንዲቀላቀሉ ገፍተዋቸዋል፡፡ ያኔ የአሁኑን መንግሥት እስካረፉበት ጊዜ ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት መለስ ዜናዊ የሽምቁንና የተቃውሞውንም የግንባር ውጊያ ለ17 ዓመታት መርተዋል፤ መለስ ወደ ሜዳ የወጡት ከዩኒቨርሲቲ ግቢ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴም እኮ ፖሊሲዎቻቸውን ይጠሉ ከነበሩ ተማሪዎች ጋር መጋፈጥ ነበረባቸው፡፡

ያዕቆብ ኃይለማርያም በ1957 - 58 ዓ.ም የኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብሄራዊ ኅብረት ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ የንጉሡ አገዛዝ ፍፁማዊ ዘውድ ቢሆንም ተማሪዎች የመሬት ሥሪትና ባለቤትነትን በመሣሰሉ ጉዳዮች ላይ ተቃውሟቸውን ማሰማት ይችሉ ነበር፡፡

“ንጉሡ በጣም አባታዊ ሰው ነበሩ፡፡ ጭካኔ አልነበረባቸውም፡፡ እኛን የሚመለከቱን በሃሣቦቻቸው ውስጥ አንዳች ኮስታራ ቁምነገር እንዳለ ሳይሆን እንደተነጫናጭ ወይም የቀበጡ ልጆች ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የበዛ እሥር አልነበረም፡፡” ብለዋል ያዕቆብ፡፡

የዛሬ ትውልድ ተማሪዎች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ በንቃት ቢሣተፉ ደስ ይላቸው እንደነበር አቶ ያዕቆብ ይናገራሉ፡፡ የአሁኖቹ ልጆች እኮ የእርሣቸው ትውልድ እንደነበረው ዓይነት ተዋጊ ወይም ተጋፋጭ ቢጤ አይደሉም - በያዕቆብ ኃይለማርያም ዕምነት፡፡

በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ተነስቶ በነበረው ተቃውሞና አመፅ ውስጥ ተማሪው የሰፋ ድርሻ ነበረው፡፡

ዘንድሮ፤ ኢሕአዴግ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ቀድሞም እንደተገመተው ሁሉ ተማሪው ምንም አላለም፡፡ ምንም፡፡ ዝም ነው ያለው፡፡

ዘገባውን ማዳመጥ ከፈለጉ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ይክፈቱ፡፡

XS
SM
MD
LG