በዓለም ላይ የተጠቃሚዎቻቸው ቁጥር እየጨመረ የመጣው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጽእኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡
ከ20 ሚሊዮን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንደሚኖሩባት በምትገመተው ኢትዮጵያም፣ ማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል፤ ሲሉ የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው ተጠቃሚዎች እና የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሰብእ ጥናት ወይም ሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህሩ አቶ አንዷለም አሰፋ፣ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች ጋራ በተያያዘ የሚከሠቱ ችግሮች በአመዛኙ በአጠቃቀም ችግር እንደሚመጣ ጠቁመው፣ ማኅበራዊ መዛነፎችም እየበዙ ነው፤ ሲሉ ያመለክታሉ፡፡