በትግራይ ክልል የአራት አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ያደረጉት ምርጫ፣ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና የጣሰ እንደኾነ የገለጸው፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ፣ እንቅስቃሴውን እንደሚቃወመው አስታወቀ፡፡
ጉባኤው፣ ለክልሉ ተወላጅ የእምነቱ አገልጋዮች፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ሰላም የሚያስጠብቅ አስተምህሮ እንዲሰጡም ጠይቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በአኵስም ከተማ ስለተካሔደው የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራርያ የሰጡት፣ የሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ዞን ሽረ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ጴጥሮስ፣ የዕጩዎቹ ምርጫ፣ ሕገ ወጥ ነው፤ የሚሉት ተሳስተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና ተከትሎ እየተፈጸመ ያለ ነው፤ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ፣ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል፣ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሔደው የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሉዓላዊነት የሚፈታተን፣ እንዲሁም ማዕከላዊ የመንበረ ፕትርክና መዋቅሯን የሚንድ ሕገ ወጥ አድራጎት ነው፤ በማለት ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁሉም አህጉረ ስብከት እንዲቃወሙትም ጥሪውን አቅርቧል፡፡የትግራይ ተወላጅ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የሚያገለግሉ አባቶችም፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚያስጠብቅ፣ አንድነትንና ሰላምን የሚያመጣ ትምህርት እና መልእክት አብዝተው እንዲያስተላልፉ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ “የቀኖና ጥሰት” ሲል በመግለጫው የተቃወመው እና “ሕገ ወጥ አድራጎት” ሲል የጠራውን ድርጊት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ አንድነትንና ሉዓላዊነትን የሚያናጋ፣ ኹለንተናዊ ቀውስም የሚያስከትል በመኾኑ፣ የፌዴራል መንግሥት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ለችግሩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው፣ የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጁ ተማፅኗል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኙ የአራት አህጉረ ስብከት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዐዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም የጀመሩትን ቀኖና አፍራሽ ሒደት አቁመው፣ ለሰላም በራቸውን ሊከፍቱ እንደሚገባ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመግለጫው አሳስቧል፡፡
የሰላም ጥረቱ ቀጥሎ ፍሬያማ እንዲኾን አስፈላጊውን ከማድረግ ባሻገር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ መብቷን በሕግ እንደምታስከብርም፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በአኵስም ከተማ ስለተካሔደው የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራርያ የሰጡት የሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ዞን ሽረ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ጴጥሮስ፣ የኤጲስ ቆጶሳቱ ምርጫ፣ በአገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ አማኞች፣ አባት ለሌላቸው አባት ለመመደብ የታቀደበት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ሒደቱ “ሕገ ወጥ ነው” የሚሉ አካላት መሳሳታቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፣ የተካሔደው ምርጫ እና በቀጣይም የሚፈጸመው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት፣ የቤተ ክርስትያኒቱን ቀኖና ተከትሎ እየተፈጸመ እንዳለ በመጥቀስ ክሡን ተከላክለዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በጦርነቱ ጊዜ ለሰላም አልቆመችም፤ እንዲሁም ጦርነቱን ደግፋለች፤ በማለ፣ በክልሉ “የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ሰላማ ላዕላዋይ ቤተ ክህነት” በሚል የራሳቸው ክልላዊ መዋቅር አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ የአገርን ሰላም እና የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅ ባላት ነባር ተቋማዊ ሚና፣ ጦርነቱ በወቅቱ እንዲቆም መግለጫ ባለማውጣቷ፣ በጦርነቱ ሒደት እና ፍጻሜ፣ በቦታው ተገኝታ
ባለማጽናናቷ እና እንዲደርስ የወሰነበትን ሰብአዊ ድጋፍ በጊዜው ማድረስ ባለመቻሏ፣ ቅሬታ እና አለመግባባት ተፈጥሯል፤ በማለት፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ የሰላም ልኡክ፣ አስቀድሞ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በደብዳቤ ባስታወቀው መሠረት፣ ወደ መቐለ ቢጓዝም፣ በክልሉ የአራት አህጉረ ስብከት ብፁዓን አባቶች እና የሥራ ሓላፊዎቻቸው አቀባበል አልተደረገም፤ እንዲሁም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጋራ በፕላኔት ሆቴል በተካሔደው የ20 ሚሊዮን ብር የሰብአዊ ርዳታ ርክክብ እና አጭር ውይይቱ፣ የክልሉ አባቶች ይኹኑ የሥራ ሓላፊዎቻቸው አልተገኙም፡፡
ይኸው ውዝግብ በቀጠለበት ኹኔታ ነው፣ በትግራይ ክልል የሚመደቡ አምስት እና ወደ ውጭ ሀገራት የሚላኩ አምስት በጠቅላላው 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም፣ የዕጩ ቆሞሳት ምርጫ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ “መንበረ ሰላማ” ተብሎ በተጠራው አካል አስፈጻሚነት በአኵስም ከተማ የተካሔደው፡፡