አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መንበረ መራሂ መንግሥቱን ከተረከቡ ወዲህ ለውጭ መገናኛ ብዙኃን አካል ቃለምልልስ ሲሰጡ ይህ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የሰጡት ልዩ ቃለ-ምልልስ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሃገር ውስጥ ጉዳዮቿ፣ በውጭ ፖሊሲዋና እንቅስቃሴዎቿ ላይ ያነጋገራቸው የቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ኃይንላይን ለአቶ ኃይለማርያም ካቀረባቸው ጥያቄዎች አንዱ ኢሕአዴግ የሕወሓት ተፅዕኖ እንዳለበት ይነገራል - የሚል ነበር፡፡
አቶ ኃይለማርያም ለጥያቄው መልስ መስጠት የጀመሩት የኢሕአዴግን የተፈጥሮ ሂደት በመተንተን ሲሆን የጥምረቱ አባል የሆኑት አራቱ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ - ሕወሓት፣ ብሔረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ብአዴን፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - ኦሕዴድ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ደኢሕዴን እንደአፈጣጠራቸውና በትግሉ ውስጥ እንዳሣለፉት ጊዜ ጥንካሬያቸው፣ አቅምና ልምዳቸው አንዱ ከሌላው እንደሚለይ አመልክተዋል፡፡
“ይሁን እንጂ - አሉ አቶ ኃይለማርያም - ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተካሄደው የሕዳሴ ሂደት አዲስና የነጠረ የፓርቲውን ፖሊሲ፣ ስትራተጂና አቅጣጫ እንዲወጣ አድርጓል፡፡…” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሉና “… በዚህም መሠረት ሁሉም ፓርቲዎች ወደ አንድ ንቅናቄ ገቡና አንድ ዓይነት አቅጣጫን፣ አንድ ዓይነት ልምድና የአሠራር አካሄድ በፓርቲው የውስጥ ሥርዓት አሠፈኑና ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል ሥፍራ ያዙ፡፡ በመሆኑም በሁሉም የኢሕአዴግ መዋቅሮች ውስጥ፤ ለምሣሌ በምክር ቤቱ ውስጥ፣ በፓርቲው ጉባዔ፣ በሁሉም ኃላፊነቶችና የሥራ ምደባዎች ላይ አራቱም ፓርቲዎች እኩል ናቸው፡፡ ለዚህ እማኙ እኔ የዚህ ሂደት ውጤት መሆኔ ነው፡፡ እኔ በሕይወት ያለሁ ማሣያ ነኝ፡፡ ኢሕአዴግ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ቡድን ተፅዕኖ ምክንያት በተ ወሰኑ ቡድኖች ወይም የጎሣ ቡድኖች ላይ የተዛባ አያያዝ አለው ብለው ለሚገምቱ ይህ የሃሰት እና ተጨባጭነት የሌለው ግምት ነው፡፡ በመሆኑም በፓርቲያችን የውስጥ ሥርዓት ውስጥ የመጀመሪያው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ግንኙት ነው፡፡ የጥንካሬአችን መሠረት የፓርቲው የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ከውጭ ሆነው የሚያስቡ፤ የሚያስቡት ፓርቲውን የውስጡን ሳያውቁ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የፓርቲውን አሠራርና ፓርቲው እንዴት እንደሚሠራ ብዥታ ላለባቸው ሰዎች ማስጨበጥ አለብን፡፡ ይህ ፓርቲ በውስጡ ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ውሣኔዎቹና ሥራዎቹ የሚከናወኑት በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ይህኛው ወይም ሌላኛው ፓርቲ ተፅዕኖ ያደርጋል፤ ወይም ይጫናል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አራቱም አባል ፓርቲዎች እኩል ቁጥር ያለው ውክልና አላቸው፡፡ ከፈለጉም በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚፈልጉት ተፅዕኖ ሁሉ አላቸው፡፡ በመሆኑም ዋናው ጠቃሚ ጉዳይ በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲ አለ፤ እየሠራ ያለ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች ያላቸውን ግምት አልቀበልም፡፡ ለማሣያም እኔ የተመረጥኩት በአራቱም ፓርቲዎች ተወካዮች በሙሉ ድምፅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእኔ ፓርቲ በደኢሕዴን ብቻ ሣይሆን በሌሎቹም ጭምር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ባይኖረን ኖሮ ለየፓርቲያችን ወገናዊ ሆነን እንቀር ነበር፡፡ በመሆኑም የእኔ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኜ መመረጥ ዘግይቶም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የዚህ ሂደት ማሣያ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ቪኦኤ፡-
በሁለት ሺህ ሰባት በሚካሄደው ምርጫ በዕጩነት ይቀርባሉ? ማለት ከዚህ ካሁኑ የሽግግር ወቅት በኋላ የፓርቲው መሪ የመሆን ተስፋ አለዎት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
የፓርቲው ጉባዔ ከመፍቀዱ በፊት፥ ለምሳሌ ልበል፥ ፕሬዚደንት ኦባማ የፓርቲያቸው አባላት ይሁንታ ሳይሰጡ “ፕሬዚደንታዊው ዕጩ እኔ ነኝ” ማለት ይችላሉ? አይችሉም። ልክ እንደዚያው ይሄም የፓርቲው ጉባዔ የፓርቲው ሂደት የሚወስነው ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ነውና። ስለዚህ ፓርቲው ያንን ዕድል የሚሰጠኝ ከሆነ እወስደዋለሁ። ካልሰጠኝ ደግሞ ሌሎች መሠራት ያለባችውን ሥራዎች እሠራለሁ ማለት ነው። የዲሞክራሲ ሂደት ስለሆነ እኔ በግሌ ተነስቼ የፓርቲው ብዙኃን አባላት ነገ የሚመጡ ጉዳዮችን በሚመለከት የሚያደርጉትን ውሣኔ እኔ አሁን ልወስነው አልችልም። ስለሆነም ይህ ለዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም። የፓርቲው አባላት ግምገማቸውን አካሂደው የሚወስኑትን “ይመርጡኛል፤ አይመርጡኝም” ብሎ ከወዲሁ መተንበይ አይቻልም።
የብዝኀ ፓርቲ ሥርዓት
ቪኦኤ፡-
ኢትዮጵያ ያለው የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ነው ሲሉ ገልፀውታል። ኢሕአዲግ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድጉ ለመቀበል በሚያስችልበት ደረጃ ለመለወጥ ምን ያህል ጊዜ የሚያስፈልገው ይመስልዎታል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
ይህም በሂደት ላይ ያለ ነው። በዚህ ጊዜ ይሆናል ብዬ የተወሰነ ቀን ላስቀምጥለት አልችልም። በሂደት የሚለወጥ ነው የሚሆነው። የእኛ ፍላጎት ግን ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ነው። ምክንያቱም በዚህች ሀገር ንቁና ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች በወጡ ቁጥር የሕዝቡም ውሣኔ የመስጠት አማራጭ የዚያኑ ያህል ያድጋልና ነው።
ለእኛ ግን አስፈላጊው የፓርቲዎች ቁጥር አይደለም። የሚያስፈልገው፥ ለሕዝብ የሚሠራው የትኛው ነው? የሕዝቦችንና የአባሎቹን ፍላጎትና ትልም የሚደግፉ ፖሊሲዎች ያሏቸው መሆናቸው ነው አስፈላጊው። ስለዚህ ይበልጥ ተመራጩ መንገድ የሚመስለኝ በሀገሪቱ ውስጥ ንቁና ጠንካራ ፓርቲዎች የመውጣታቸው ጉዳይ ነው። ያም ሲሆን ነው የአንድ ፓርቲ የበላይነት ከሌሎቹ ጋር አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ እና ሕዝቡ የፈለገውን ለመምረጥ ዕድል ሊሆን የሚችለው። ይህ ማለት ግን ኢሕአዴግ የበላይነቱን ያጣል ማለት አይደለም። የሕዝቡ ምርጫ ነው ወሣኙ። ስለዚህ አንዳንድ የአውሮፓ ፓርቲዎችን ብናይ ለሃምሣና ስልሣ ዓመታት በበላይነት የቆዩ ናቸው። በጃፓንም እንዲሁ ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል። ስለዚህም ኢሕአዴግ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ሩጫ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለረዥም ዓመታት ሊቆይ ይችላል። እንዳልኩት ግን ሁሉም በሂደት የሚለወጥ እንጂ ቀን ሊቆረጥለት የሚችል አይደለም፡፡
የመረጃ ፍሰትና ሃሣብን የመግለፅ ነፃነት
ቪኦኤ፡-
ኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ወይም መረጃ ፍሰትን በጥብቅ ትቆጣጣራለች ተብላ በአንድአንድ አካባቢዎች ትነቀፋለች። ነቀፋ የሚያቀርቡ ጋዜጦች ተዘግተዋል፤ ጋዜጠኞች ፀረ-ሽብር ህግ በመተላለፍ ተወንጅለዋል፤ ዌብሳይቶች ይዘጋሉ፤ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ሥርጭትም ሳይቀር ይታፈናል፤ የውጭ ሥርጭቶች ይታፈናሉ። የርስዎ መንግሥት በተለይ ትላልቆቹን ጉዳዮች በተመለከተ እንደተዘጋው ፍትህ ጋዜጣ እና የታሠረውን በጣም ነቃፊ የሆነ የብሎግ ጋዜጠኛ እክንድር ነጋን የመሣሱትን ጉዳዮች አስመልክቶ የርስዎ መንግሥት ምን ያደርጋል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
ጓደኞችህ እንደሆኑና ስለእነርሱም የሚሰማህ ሕመም ሊኖር እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ፒተር! መረዳት ያለብህ፣ ሁለት ቆብ ያለው ማንም ሰው ሁለት ቆብ ማጥለቁን ማቆም አለበት፡፡ አንዱን ብቻ ነው ማድረግ ያለበት፡፡ እነዚህ ሁለት ቆቦች አንዱ በሕጋዊ መንገድ መንቀሣቀስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሕገወጥና የሁከት መንገድ፤ ከአመፀኛ ድርጅቶች ጋር መሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሠሩት ሰዎች የታሠሩት ወይም የተከሰሱት በሕጋዊ መንገድ በመንቀሣቀሣቸው አይደለም፡፡ የታሠሩት ሰዎች ከአመፅ አራማጅ ድርጅቶች ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ በጋዜጠኝነት ሥራቸው ምክንያት አይደለም የታሠሩት፡፡ ይህ የተፈቀደ ነው፡፡ ታውቃለህ፤ አንተ እዚያ ነበርክ፤ እዚያ ሠርተሃል፤ ነገር ግን ቀዩን መሥመር ማለፍ የለብህም፡፡ አመፅ ቀስቃሽና የሽብር ፈጠራ ድርጅቶችን ማገዝን የመሣሰሉ አድራጎቶች ውስጥ መግባት የለብህም፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኝነት አይደለም፡፡ ተቃዋሚ መሆንም አይደለም፡፡ ተቃዋሚ በሁከትና በሕገወጥ መንገድ አይንቀሣቀስም፡፡ ከሽብር ፈጠራ ቡድኖች ጋርም አይገናኝም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች አይደሉም፤ ግለሰቦች ናቸው፡፡ እኛ ማንኛውንም ፓርቲ አልከሰስንም፡፡ ምክንያቱም በሕጋዊነት የተመዘገቡት ፓርቲዎች በሃገሪቱ ውስጥ በሕጋዊነት መንቀሣቀስ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ በአባልነት የተመዘገቡ ግለሰቦች፤ ግን ሁለት ምዝገባ ያላቸው፤ አንዱ በሕጋዊ ፓርቲዎች ውስጥ፣ ሌላው ምዝገባ በሕገወጥና የሽብር ፈጠራ ፓርቲዎች ውስጥ የሆነ የሚከሰሱት በሕጋዊው ቆባቸው ሳይሆን በሌላኛው፣ በሕገወጡና ከሽብር ፈጠራ ጋር በተያያዘው ቆባቸው ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን መለየት አለብን፡፡ በግልፅና ያለአንዳች ማወላወል ካቆሙና በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት ከወሰኑ ሁልጊዜ መድረኩ አለ፡፡ ሁለቱንም የሚቀላቅሉ ከሆነ ሁለቱን ለይተን፤ ለሕገወጡ፣ ለአመፅና የሽብር ፈጠራ ግንኙነታቸው እንከስሣቸዋለን፡፡ ይህ በሃገሪቱ ሕግ መሠረት ይያዛል፤ ያስቀጣልም፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ግንዛቤ ሊጨበጥባቸው ይገባል፡፡ ለእናንተ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይህ ችግር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኞች በሕገወጥ መንገድ አይንቀሣቀሱም፡፡ የሚሠሩት በሕጋዊ መንገድ ነው፤ ያላቸውም አንድ ቆብ ብቻ ነው፡፡ በዚህና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነት ይኸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ምዕራብ ሃገሮች ይህንን ቅልቅል አይረዱም፡፡ ምክንያቱም ችግሩ የለባቸውም፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች በሕጋዊ መንገድ ሲሠሩ ነው የሚያዩት፡፡ ይህ የሕገወጡና የሌላኛው ቆብ ችግር የለባቸውም፡፡ ያ ልዩነት አንድንዴ ብዥታ ያለበት ነው፡፡ እኛን በሚመለከት በቅድሚያ የምናተኩረው በብሔራዊ ፀጥታ ጉዳዮቻችን ላይ ነው፡፡ ይህ የብሔራዊ ደህንነት ጥቅም ጉዳያችን ደግሞ አንድ ሰው ሁለት ቆብ ስላለው ብቻ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሣቀሱ እንመክራቸዋለን፡፡ በጋዜጠኝነትም ቢሆን፣ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ፡፡
ቪኦኤ፣-
ባሁኑ ጊዜ መንግሥትዎ የፕሬስ ነፃነትን ምናልባት ትንሽ ለቀቅ ማድረግ ላይ ምን አቋም አለው? ባሁኑ ጊዜ ዌብሳይቶች ተዘግተዋል፤ የውጭ ሥርጭቶች ታፍነዋል፤ ጋዜጦች ተዘግተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
ግልፅ መሆን ያለበት የእኔ መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች የማገድ ፖሊሲዎች የሉትም፡፡ የሚወሰነው በዌብ ሣይቶቹም ይሁን በማንም፤ በማንነታቸው ነው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ድርጅቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ካላቸው፣ ግልፅ ነው፤ ያ በሁሉም ሃገር ውስጥ ይደረጋል፡፡ የኦሣማ ቢን ላደንን ብሎግ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መክፈት አትችልም፡፡
የውጭ ጉዳዮች:-
የአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት
የውጭ ፖሊሲ - ሲል ፒተር አቶ ኃይለማርያምን ስለ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ስምምነት የሚከተለውን ጠይቋል፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ሲደራደሩ ነበር፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለድርድሩ ባደረጉት አስተዋጽዖ በጣም ሲመሰገኑ ነበር፡፡ እርስዎ ጉዳዩን ይከታተሉ ነበር?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
መልካም ዕድል ሆኖ ልክ ከአምስት ደቂቃ በፊት ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት። ይህን ጥያቄ ስላነሳህ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ስምምነቱ ሲካሄድ ኒው ዮርክ ሆኜ በቀጥታ ስከታተል ነበር።
ስምምነት ላይ ደርሰው ተፈራርመዋል። እንደሚታወቀው ፖሊሲአችን ከቀድሞው ያልተዛነፈ ነው። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲፀናም አስተዋጽዖ አድርገዋል። ስምምነቱን ለማሣካት ትልቅ ጥረት አድርገዋል፤ ድጋፋቸው፣ የማደራደር ችሎታና ስልታቸው ውጤታማ ሆኗል። የርሳቸው ህይወት ካለፈ በኋላ ፈለጋቸውን በመከተል ከሁለቱም ሱዳኖች መሪዎች ጋር ስሠራ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለድርድሩ ጥሩ መሠረት ስለጣሉ ኢትዮጵያ ተደማጭነት አግኝታለች። ለዚህም የደቡብና የሰሜን ሱዳን መሪዎችን አመሰግናለሁ።
መሪዎቹ ከአብዬይ ጉዳይ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል በሁሉም ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል። የአብዬይ ጉዳይም የአፍሪቃ ህብረት ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ኃላፊነት እንዲወስድና ውሳኔውን እንደሚቀበሉ ተስማምተዋል።
የእኛ ፖሊሲ ለአፍሪቃ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ብልፅግና እንዲሰፍን ለትብብር መሥራት ነው። እንደ ኢጋድ ሊቀ መንበርም ዓላማችን ይህ ነው። መልካም ዕድል ሆኖ ሶማሊያም የሽግግር ጊዜዋን አብቅታ ብቁ ፕሬዚደንት መርጣለች። ፓርላሜንታዊ ሥርዓት አስፍና በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ኢኮኖሚዋን እንደምታዳብር ተስፋ አለን።
በኤርትራ ጉዳይ
ቪኦኤ፡-
ለኢትዮጵያዊያን አነጋጋሪ ሆኖ የቆየውና የሚያሳስባቸው የውጪ ፖሊሲ ኤርትራን የሚመለከተው ነው። ይህ ለኢትዮጵያዊያን ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በቅርቡ እርስዎ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሠላምታ በመለዋወጥ እንደተጨባበጡ ይነገራል፡፡ ስለዚያ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ግን እውነት ከሆነ እርስዎ ይነግሩናል፤ ምናልባትም እንደገና ድርድር ለመጀመር እርምጃ አለ ይባላል። የኤርትራውን መሪ አነጋግረዋል? የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል ሂደት ተጀምሯል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
አመሠግናለሁ፤ ፒተር! ኤርትራን በሚመለከት ያለንን የውጭ ፖሊሲ አልለወጥንም፡፡ ፖሊሲያችን ጦርነቱን ተከትሎ የተቀረፀና ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት እየሠራ ያለ ፖሊሲ ነው፡፡ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መነጋገር እንፈልጋለን፡፡ ግንኙነታችንን ልናሻሽል የምንችልበት ብቸኛ መንገድ ንግግር ነው፡፡ ይህንንም ለኤርትራ መንግሥትና መሪዎች አሣውቀናል፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ይሆናል ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ ወደፊትም በዚሁ እንቀጥላለን፡፡ የፖሊሲ ለውጥ የለንም፤ የፖሊሲውን አቅጣጫም ያወጣነው እኛው ነን፡፡ እኛ የምንለው ባለአምስት ነጥብ የሠላም ሃሣብ፣ የሠላም ስትራተጂ ነው፡፡ አሁንም ጠረጴዛ ላይ ያለ ነው፡፡ ግንኙነቶቻችንን ለማሻሻል ከኤርትራ መንግሥት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን መነጋገር እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ አሁንም ሂደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
መጨባበጥን በተመለከተ ግን እኛ ኤርትራ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ችግር የለብንም፡፡ የአገዛዙ ችግር ነው፡፡ ተደርጎም ከሆነ ችግር የለውም፡፡ ግን አልተጨባበጥንም፡፡
አባይ፣ ግብፅና ሱዳን
ቪኦኤ፡-
ቀጥሎ የማቀርብልዎ ጥያቄ ግብፅን የሚመለከት ነው። እርስዎ እስካሁን የሠሩት በሥርዓተ-ትምህርት ዘርፍ ነው። ካልተሣሣትኩ በውኃ ምኅንድስና ዲግሪ አለዎት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአባይን ወንዝ በጋራ ስለመጠቀም ተወስቷል፡፡ ይህም በካይሮና በአዲስ አበባ መካከል ውጥረት ፈጥሯል ይባላል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የግብፅ ባለሥልጣናት ‘ኢትዮጵያ በውኃው አጠቃቀም ላይ አክራሪ አቋም ይዛለች’ ሲሉ በይፋም ባይሆን በሚስጥር መናገራቸው ተሰምቷል። በዚሁ ሰሞን ደግሞ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1995 ዓ.ም በቀድሞው በፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ግድያ በመሞከር ወንጀል ተፈርዶባቸው ኢትዮጵያ እሥር ቤቶች ውስጥ ስለሚገኙ ግብፃዊያን ጥያቄ መላኩን አስታውቋል። እነዚህ ሁሉ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና የመመልከት አዝማሚያ ይጠቁማሉ፡፡ መጀመሪያ በእሥረኞቹ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት? በተጨማሪ ደግሞ እርስዎ የሚመሩት መንግሥት በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ከቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር የተሻለ የሚባል አግባብና ለዘብተኛ አቋም ሊኖረው ይችላል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
በቅድሚያ ፒተር፤ የአባይን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያና የግብፅን ግንኙነት በሚመለከተው የውጭ ፖሊሲ ጉዳይ ላይ የውኃ መሃንዲስ መሆን አያስፈልግህም፡፡ ምክንያቱም ይህ ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የአባይ ጉዳይ ለምዕት ዓመታት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መንግሥት ብቻ ሣይሆን በቀደሙ የኢትዮጵያ መንግሥታትም፣ እንዲያውም በግብፅም ከፈርዖን ዘመናት ጀምሮ ያለና እየቀጠለ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የአትዮጵያ ብቻም የሆነ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሁሉም የአባይ ተፋሰስ ሃገሮች ጉዳይ ነው፡፡ የተፋሰሱ የራስጌም ሆነ የግርጌ ሃገሮች ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዓለምአቀፍ ጉዳይም ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ ከግርጌዎቹ ሃገሮች ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ለመስማማት ልበ ሰፊ ሃገር ሆና ቆይታለች፡፡ ከግብፅ ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ውኃውን በጋራ የሚጠቀሙት እነርሱ ናቸው፡፡ አሁን ታዲያ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ያለን ሃገሮች የውኃው ተቀራራቢ ተጠቃሚ እንድንሆን የራስጌዎቹ ሃገሮች ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
ይህ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለአባይ 86 ከመቶውን ውኃ የምታስገባ ሃገር ነች፡፡ ይህንን ውኃ ታዲያ ‘ኢትዮጵያ ለልማቷ ልታውለው አትችልም’ የምትል ከሆነ ይህ የቂል ሰው ስሌት ነው የሚሆነው፡፡ ካለበለዚያ ይህ እጅግ ቀላልና አመክኗዊ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የግድ የውኃ ኢንጂነር መሆን የለብህም፡፡
ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በግርጌዎቹ ሃገሮች፣ በሱዳንና በግብፅ ላይ አንዳችም የጎላ ጉዳት ሳይደርስ ውኃውን መጠቀም ትፈልጋለች፡፡ በቴክኒክ ደረጃም እነዚያን የግርጌ ሃገሮች ሳንጎዳ የራስጌዎቹ ሃገሮች ተጠቃሚ ልንሆን እንችላለን፡፡ ይህ መፍትሔ እስካለን ድረስ ለምን አንተባበርም? በመሆኑም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ለኃይል ማመንጫ የሚውሉ ግድቦችን መገንባት ጀመረች፡፡ ይህ ደግሞ ውኃውን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚወስደው ወይም የሚያስቀረው አይደለም፡፡
በተጨማሪም በሱዳን፣ በግብፅና በሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚ ለማሳደግም አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡ በመሆኑም ይህ ሁሉም አሸናፊ፣ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትና ነገሮችን በትብብር መሥራት የሚቻልበት መስክ በመሆኑ ሁላችንም ወደ ትብብሩ መምጣት አለብን፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በጣም ግልፅ የሆነና መታየት የሚችል ሃሣብ ለግብፅና ለሱዳን አቅርባ የሱዳን፣ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ያሉበትን አንድ ቡድን ለማቋቋም ተስማምተናል፡፡
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በግብፅና በሱዳን ላይ የሚደርስ ጉዳት መኖር አለመኖሩን የሚከታተሉ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎችም ተካትተዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያና ያለፉ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሃሣብ የሚያመለክተው አብረን የመሥራትና የማደግ መንገድን ለመሻት ያለንን ብርቱ ፍላጎት ነው፡፡
አባይ፣ አብረን ለማደግ አብረን መሥራት የምንችልበት ብቸኛው ጉዳይ አይደለም፡፡ አባይ፣ ለዲፕሎማሲያችንና ለምጣኔ ኃብት መቀናጀት መሠረታዊና ማዕከላዊ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ብቸኛው መንገድ አይደለም፡፡ መናገድ እንችላለን፤ አንዱ በሌላው ሃገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ይችላል፤ በሕዝቦች ግንኙቶች ላይ መሥራት እንችላለን፡፡ ግንኙነቶቻችንን ከግብፅና ከሱዳን ጋር በብዙ መንገዶች ማጠናከር እንችላለን፡፡
ችግሩ የቀደመው የግብፅ መንግሥት ነበር፡፡ የአሁኑ መንግሥት ምን እንደሚያደርግ ሰንብተን እናየዋለን፡፡ ያለፈው ግን የአባይን ጉዳይ የሚያየውና የያዘውም እንደፀጥታ፣ እንደደህንነት ጉዳይ ነበር፡፡ የውጭ ዲፕሎማሲ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ጉዳይ አልነበረም፡፡ የአባይን ጉዳይ የያዘውም የደህንነት ኃላፊው ነበር፡፡
አሁን እየተሰሙ ያሉ ጭምጭምታዎች አሉ፡፡ ‘የደህንነት ጉዳይ ነው፤ ግብፅ እንደደህንነት ጉዳይ ነው የያዘችው’ የሚሉ፡፡ ይሁን እንጂ እኔ የአሁኑን መንግሥት አቋም አሁን ልነግርህ አልችልም፡፡ የሽግግሩ መንግሥት ከእኛ ጋር ቆሞ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ መሪዎችም የአዲሱ መንግሥት አባል ናቸው፡፡ በቅርብ እየተከታተልነው ነው፡፡ ምክንቱም በዚህ ጉዳይ ላይ የሠሩ ባሉት ቡድኖች ላይ የተፈጠረ ችግር የለም፡፡ አሁን ያለው የተሣካና የተጣጣመ የሥራ ግንኙነት ነው፡፡
የእኛ ጉዳይ ግን አባይ ላለመተማመን ምክንያት መሆን የለበትም የሚል ነው፡፡ አብሮ የመሥራት፣ የመተማመንና የመተባበር፣ የጋራ ጥቅም፣ አብሮ የማደግና ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበት መፍትሔ ጉዳይ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ ይህ ደግሞ ይቻላል፡፡ ለዚያም እንሠራለን፡፡ መጋጨት አያስፈልገንም፡፡ ስድስት ሺህ ሜጋዋት ኃይል ካመነጨን በደጋማው መልክአምድራዊ አቀማመጧ ምክንያት ኢትዮጵያ ከተጎናፀፈችው ፀጋ የሚወጣውን የውኃ ኃይል ማስተባበር ማቀናበርና ማገናኘት፣ ከዚያም ሁላችንም ተጠቃሚ መሆን እንችላለን፡፡ ይህ ነው የሚፈለገው፡፡
ሱዳንን ብትመለከት፣ በዚህ ግድብ ምክንያት ሱዳን የተገራ ውኃ ማግኘት ትችላለች፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ስትነፃፀር ሱዳን ለግብርና ልታውል የምትችለው በቂ ስፋት ያለው መሬት አላት፡፡ ይህም በራሱ ፀጋ ነው፡፡ ሱዳን ውስጥ በመስኖ የሚለማ ግብርና ካለ፤ ከውጤቱ ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን ማለት ነው፡፡ በግብፅም እንዲሁ፡፡ በመሆኑም አብሮ የመሥሪያ እንጂ የፀጥታና የደህንነት ጉዳይ አድርገን ልንይዘው አይገባም፡፡ የአባይ ምሥራቅ ተፋሰስ ሃገሮች፤ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ሕዝቦች በጋራ የምንለማበት ጉዳይ ነው ማድረግ ያለብን፡፡ አሁን በግምት መመራት አንፈልግም፤ ለጊዜው አሁን ባለው የግብፅ መንግሥት ዘንድ የፖሊሲ ለውጥ አላየንም፡፡
ቪኦኤ፡-
ግብፃዊያን እሥረኞቹን አስመልክቶ ስላቀረቡት ጥያቄስ መልስዎ ምንድነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
ይህ ባለፈው መንግሥት የተዘጋ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ አየህ! የሽብር ፈጠራ አድራጎቶች በማንኛውም መልክ ቢሆን አይመከሩም፤ ተቀባይነትም የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የቀድሞውን የግብፅ ፕሬዚዳንት ለመግደል በሞከሩት ላይ የሞት ቅጣት ፈርዶባቸዋል፡፡ ይህ ባለፈው መንግሥት የተዘጋ ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ወቅት የምንመለስበት ምክንያት የለም፡፡
ርዕዮተ-ዓለም፣ ቻይና፣ አሜሪካና ሌሎች
ቪኦኤ፡-
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙውን ጊዜ ቻይናን “በኢኮኖሚ እምርታ እያሣየች ያለች” እያሉ በአድናቆት ይገልፁ ነበር። ምዕራባዊያን አገሮችን ደግሞ እየወደቁ ያሉ ኃይሎች ሲሉ በመግለፅ ነቀፋ ያሰሙ ነበር። ኢህአዴግ ከቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ጋር ስላለው ቅርበት በሰፊው አስታውቀዋል። ምዕራባዊያን ኢኮኖሚአቸው እየወደቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርዕዮተ-ዓለም ቅርበት ካላትና ታዳጊ የኢኮኖሚ ኃይል እየተባለች ካለችው ቻይና ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር ይሻላታል ብለው ያምናሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-
ከሁሉም በፊት ከሃገሮች ጋር ያሉን ግንኙነቶች የሚመሠረቱት በርዕዮተ-ዓለም ጉዳይ ላይ አይደለም፡፡ ከግንኙነቶቹ በምናገኛቸው ጥቅሞች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እንደዚሁ ዓይነት ጥያቄ ከዚህ በፊትም ጠይቀኸኝ የመለስኩልህ በተመሣሣይ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም ከዩናይትድ ስቴትስም፣ ከቻይናም ጋር ያሉን ስትራተጂካዊ ግንኙነቶች ናቸው፡፡
ይህ ስትራተጂካዊ ግንኙነት ተነጥሎ የተወሰደን ሃገር ባነሣህ ቁጥር የራሱ የሆኑ ደርዞች አሉት፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር በምጣኔ ኃብት ልማት በኩል በጣም የቅርብ አጋር ነች፤ በተለይ ግብርናን፣ የጤና ዘርፍና ሰብዓዊ ድጋፍን በመሣሰሉ ጉዳዮች ላይ፡፡ ይህ ግዙፍ ድጋፍ ነው፡፡ ለዚህ ድጋፍ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስን ሕዝብና መንግሥት እናመሠግናለን፡፡ በአካባቢያችንና በዓለም አቀፍ ደረጃም ሠላምና ፀጥታን በሚመለከት ስትራተጂያዊ ወዳጆች ነን፡፡ የሃያዎቹን ከበርቴ ሃገሮች፣ የስምንቱን ሃያላን ሃገሮች ቡድኖች በመሣሰሉት መድረኮች ላይ ፍትሕ የሰፈነበት፣ ተመጣጣኝ ክፍፍል ያለበት ዓለም እንዲኖር፣ በአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም ጉዳዮችን በተመለከተ አብረን እንሠራለን፡፡ በመሆኑም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባለን ግንኙነት ዓለምአቀፍ፣ አካባቢያዊና የሁለታችን የሆኑ የጋራ ሥራዎች አሉን፡፡
ሁለተኛ - ቻይና፡፡ ቻይና ስትራተጂያዊ ወዳጃችን ነች፡፡ በመሠረተ-ልማት፣ በመዋዕለ-ነዋይ ታግዘናለች፡፡ ብዙ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከዩናይትድ ስቴትስና ከአውሮፓ የሚመጣውም የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ጨምሯል፡፡ ይህንን በተመለከተ እኛ ለርዕዮተ-ዓለም ጨርሶ ዐይን የለንም፡፡ ከሃገሮች ጋር ግንኙነቶችን እንድንመሠርት የሚያደርጉን ለሕዝባችን የሚጠቅሙ፣ ለሃገራችን የሚጠቅሙና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮቻችን ናቸው፡፡ ዲፕሎማሲያችን ግልፅ ነው፡፡ የውጭ ግንኙቶታችን ድብቅ ነገር የላቸውም፤ ዘልቀው የሚታዩ ናቸው፡፡ መሠረታቸው ርዕዮተ-ዓለም አይደለም፡፡
ፓርቲያችን ከቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ጋር የቅርብ ትሥሥር አለው፡፡ ምክንያቱም የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ እያከናወነ ካለው ልንማራቸው የምንችላቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በአጭሩ እኛ ያለን ፖሊሲ ሕዝብን መሠረት ያደረገ እና ልማትን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ እታች ወርዶ በመሥራት የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ልምድ አለው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን አያያዝ ከቻይና እንማራለን፡፡ ይህ ማለት ግን ርዕዮተ-ዓለማችን ከቻይናው ጋር ተመሣሣይ ነው ማለት አይደለም፡፡ ከሁሉም ሃገር፣ ከሁሉም ፓርቲ የምትማራቸው የተሻሉ ልምዶች አሉ፡፡ እንደምታውቀው እኛ ግራ ዘመም ፓርቲ ነን፡፡ እኛ ከቻይና ጋር ብቻ ሳይሆን ከጀርመኑ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጋርም በዚሁ ግራ ዘመም አመለካከታችን ምክንያት እንሠራለን፡፡ ከኤኤንሲ ጋር እንሠራለን፡፡ ከሌሎችም የአውሮፓ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ጋር እንሠራለን፡፡ ከእንግሊዙ ሌበር ፓርቲ ጋርም እንሠራለን፡፡ ከአንዱ ወይም ከሌላው ትማራለህ፡፡
እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሣችን ርዕዮተ-ዓለም እንዳለን ነው የሚሰማን፡፡ የራሣችን ነው፤ ብሔራዊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአንዳንዶች ወይም ከሌሎች ጋር ተመሣሣይ ጎኖች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ለፓርቲያችን ሚጠቅሙ ሆነው የምናዘምባቸው ጉዳዮች ካሉ እንማርባቸዋለን፤ ልምድ እንቀስምባቸዋለን፡፡ እንዳለ እንወስዳቸዋለን ማለት ሳይሆን ከራሣችን ሁኔታ ጋር ማዛመድ የምንችልበትን መንገድ እንፈልጋለን፡፡ በሃገር ደረጃ፣ በፓርቲው የውስጥ አሠራሮች ውስጥ፣ በዓለም ውስጥ ካሉ ሶሻሊስት ዓለምአቀፍ አባል ከሆኑ ፓርቲዎች ሁሉ ጋር መሥራት እንፈልጋለን፡፡ በአውሮፓ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በቻይናና በሌሎችም የዓለማችን አካባቢዎች አሉ፡፡
/ተፈፀመ/