በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ


ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈትና ዕሁድ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከተፈፀመው የአስከሬናቸው ቀብር በኋላ ኢትዮጵያ ወደፊት መመልከቷን ጀምራለች፡፡

please wait

No media source currently available

0:00 0:07:57 0:00
ቀጥተኛ መገናኛኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ ምን ልትመስል እንደምትችል የምሥራቅ አፍሪካ ሪፖርተራችን ጌብ ጃሰሎ ዘገባ ይፈትሻል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ “ኢትዮጵያ በቅርብ ዘመናት ታሪኳ አይታው በማታውቅ ሁኔታ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የማድረግ ተስፋ ይዛለች” ይላል የአዲስ አበባዋ ዘጋቢያችን ማርቴ ፋን ደር ቮልፍ የላከችው ዘገባ፡፡

ይሁን እንጂ ኃይለማርያም ደሣለኝ ቃለ መሃላ የሚፈፅሙበት ዕለት እስከአሁን ግልፅ አይደለም ትላለች ማርቴ፡፡

ከረዥም ጊዜ መሪዋ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ለሁለት ሣምንታት ያህል ኀዘን የነበረባት የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ወደመደበኛ ሕይወቷ እየተመለሰች ነው፡፡

መለስ ከሃያ ዓመታት በላይ በዘለቀው የሥልጣን ዘመናቸው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቀጥሎ፣ መለስ በሌሉበት ምን ይመጣ ይሆን? የሚል ጥያቄ ከብዙዎች ይሰማል፡፡

የመለስ ምክትል ሆነው የቆዩት ኃይለማርያም ደሣለኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይተኳቸዋል እየተባለ ነው፡፡ በቅድሚያ ግን ቃለ መሃላ መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡

ከመለስ ኅልፈት ከሁለት ቀናት በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ቃለመሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ተነግሮና ተጠብቆም የነበረ ቢሆንም በኀዘኑ ምክንያት በሚል ሥነ-ሥርዓቱ መተላለፉ ይታወሣል፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - ኢዴፓ መንግሥቱ በአፋጣኝ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኖረው ጠይቋል፡፡

የፓርቲው ዋና ፀሐፊ መስፍን መንግሥቱ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል የሌሎች አፍሪካ ሃገሮች በቅርብ ጊዜ የወሰዱትን እርምጃ “ጋናና ማላዊን በመሳሰሉ ሌሎች ሃገሮች ውስጥ በቅርቡ ያየነው ወደ ሌሎች ጉዳዮች ከመግባታቸው በፊት ወዲያውኑ አዲስ ፕሬዚዳንት መሰየማቸውን ወይም ምርጫ ማካሄዳቸውን ነው፡፡ እዚህ እኛ እያየን ያለነው ግን ከዚያ ጋር ጨርሶ የሚቃረን ነው፡፡” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

የመንግሥቱ ቃል አቀባይ በረከት ስምዖን ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኅልፈት ተከትሎ ሰጥተውት በነበረ መግለጫ እስከ 2007ቱ ምርጫ ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረው ነበር፡፡

“የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይዘን እንድንቀጥል ይፈቅድልናል፡፡ ለአሁን ተጠባባቂ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፤ በቀጣይነትም ፓርላማው ሥራቸውን ያስቀጥላቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡

ለጊዜው ግን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመንግሥቱ መገናኛ ብዙኃን አሁንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ በውኑ ግን ኃይለማርያም ደሣለኝ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሠላማዊ የሥልጣን ርክክብ ይሆንና በታሪኳም አዲስ ምዕራፍ ይገለጣል ማለት ነው፡፡

ይህ ሠላማዊ ሽግግር ለኢትዮጵያና በአመፅ ለተመላውም ታሪኳ አንድ ግዙፍ እርምጃ ይሆናል ይላሉ በኢትዮጵያ ላይ የታሪክ መፅሐፍትን የሚፅፉት ፓትሪክ ጊልከስ፡፡ “ይህ በብዙ መንገድ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተጓዘች ያሣያልና፡፡ አሁን እየሠራ ያለ አስተዳደራዊ መዋቅር አላት፡፡ ባለፉት ሃያ አስቸጋሪ ዓመታት ያካበተችው ልምድ ወደተዋጣለት የፌዴራላዊ መዋቅር ሥርዓት እንድትሸጋገር ለማድረግ በጣም ይጠቅማታል፡፡ የየራሣቸው ምክር ቤቶችና የየራሣቸው አስተዳደራዊ መዋቅር ያላቸው የክልል መንግሥታት አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ማንኛውንም ዓይነት መረባበሽ፣ ችግሮችና አደጋዎችን መቋቋም የሚችል መዋቅር ተዘርግቷል ማለት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

አሁን የሚባለው ሽግግር ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ሲታይ የተለየ መሆኑን ተንታኙ መድኃኔ ታደሠ ይጠቁሙና ይሁን እንጂ ያ ሽግግር የሚባለው ቃል በውኑ ያለውን ሁኔታ እንደማይገልፀው እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፤ “ይህ ከገዥ ፓርቲ ለተቃዋሚ ፓርቲ የሚተላለፍ የሥልጣን ሽግግር አይደለም፡፡ በተቋሙ ውስጥም ይሁን ከውጭ ተተኪውን ሊፈታተን የሚችል ኃይለኛ ወይም ጠንካራ ነው የሚባል ቡድን የለም፡፡ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው እውነተኛውን የፖለቲካ ሽግግር አይደለም፡፡”

ይህ ሽግግር ወይም ርክክብ የኢትዮጵያን የአመፅ ታሪክ ይቀይረዋል? እየቆየን የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ ርክክቡ ሠላማዊ እንዲሆን ብዙ ኢትዮጵያዊያን በብርቱ ቢሹም ወደፊትም ሠላም ይሠፍን፣ በሠላም መዝለቅም ይቻል ዘንድ ብዙ ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው የሚመክሩት መድኃኔ “በፀጥታና በልማት ብቻ ሣይሆን በፖለቲካና በሲቪል መብቶች ደረጃም፣ በሁሉም መስኮች ለውጦችን እስካላመጡ ችግር ይኖራል፡፡” ይላሉ፡፡

መንግሥቱ ግን የፖለቲካ ለውጦችን ያመጣል የሚል አንዳችም ፍንጭ የለም፡፡ ባለሥልጣናቱ የመለስን ፖሊሲዎች ይዘው እንደሚጓዙ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

መለስ ለተቃውሞ ብዙ ቦታ አይሰጡም ነበር፡፡ መንግሥታቸው ተቃውሞ የሚያሰሙ ጋዜጠኞችንና ተሟጋቾችን በተደጋጋሚ ሲያሥር ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ መሪዎች ይህንን አያያዝ በቅርቡ የሚለውጡ እንደማይመስሉ ተንታኙ መድኃኔ ታደሰ ይናገራሉ፡፡ “ወደፊት፣ በተራዘመ ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ በቅርቡ ግን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም መንግሥቱ እንዲያውም መተማመን በማጣት ምክንያት ይበልጥ አፋኝ ካልሆነ በዚሁ የመቀጠል ባሕርይ ነው የሚኖረው፡፡ አሁን ምን እንደሚጠብቃቸው አያውቁም፡፡” ብለዋል፡፡

ኃይለማርያም ደሣለኝ በዚህ ሣምንት መጨረሻ አካባቢ ሥልጣኑን በይፋ ይረከባሉ እየተባለ ነው፡፡ ኃይለማርያም ደሣለኝ ሥራውን በሙሉ አቅም እየሠሩ ናቸው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡
“ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነቱን እንዲረከቡ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ ምክንያቱም በሕገመንግሥቱ የሠፈረ ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስሩ በሌሉበት እርሣቸው ናቸው ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ አሁን በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወስኑት እርሣቸው ናቸው፡፡” ብለዋል አቶ ዲና፡፡

አሁን ጥያቄው መለስን እንዲያ ያገዘፋቸውን ሰፊ ድጋፍ ኃይለማርያም ማግኘት ይችላሉ ወይ? ነው፡፡

ኃይለማርያምን የሚጠብቃቸው ሌላው ፈተና የወጡት ከትግራይ አለመሆኑ ነው፡፡ የዚያ ጎሣ አባላት ጦሩን ጨምሮ አብዛኞቹን ተቋማት ይቆጣጠራሉ፡፡

በዋና ከተማይቱ ውስጥ የሚሰማው ጭምጭምታ ደግሞ ኃይለማርያምን ወደጎን ሣያገልሏቸው አይቀሩም የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት አይደለም የሚሉት ዲና ሙፍቲ “በፓርቲው ውስጥ የርስ በርስ ፍጭትና መናቆር አለ የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ ይህ ጀማሪ ፓርቲ አይደለም፡፡ በጣም ጠንካራ ፓርቲ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

መለስ ዜናዊ የሃገሪቱን ልማት በዓመታት አስቀድመው በማቀድ የሚታወቁበት ለኢትዮጵያ ወደፊት ተቀርፆ የተቀመጠ ራዕይ ነበራቸው፡፡ ከኅልፈታቸው በኋላም ወደተግባር ያስገቧቸው ፖሊሲዎቻቸው ሃገሪቱን ወደ መልካምም ይሁን ወደከፋው መለወጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG