በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ መንገድ ያጡ ኢትዮጵያውያን አጣብቂኝ ገብተዋል


ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ መንገድ ያጡ ኢትዮጵያውያን አጣብቂኝ ገብተዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:20 0:00

ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ መንገድ ያጡ ኢትዮጵያውያን አጣብቂኝ ገብተዋል

በጦርነት በተበታተነችው በየመን ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች፣ ገቢ ለማስገኘት የሚያስችል ሥራም ኾነ ወደ አገራቸው መመለሻ መንገድ ማጣታቸውና በአጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ተገለጸ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት፣ በክልሎቹ ባለው የጸጥታ ችግር የተነሳ፣ ከዐማራ ወይም ከትግራይ ክልል ወደ የመን የመጡ ፍልሰተኞችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመኾኑ፣ ውሳኔውን የተቃወሙ ስደተኞች ወደ አደባባይ እንዲወጡ ምክንያት ኾኗል።

በፈቃደኝነት ከየመን ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ስደተኞች የሚቀርበውን ሰብአዊ ርዳታ የሚቆጣጠረው ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM)፣ በቅርቡ፣ በክልሎቹ ባለው የጸጥታ ችግር ሳቢያ፣ ወደ ትግራይ እና ዐማራ ክልሎች የሚመለሱትን ስደተኞች ማጓጓዝ እንዳቋረጠ ታውቋል። ድርጅቱ፣ ከስደት ተመላሾቹ ወደ አገራቸው የመመለስ ጉዞን ማስቆም ባይችልም፣ ሊመለሱ የሚችሉበትን ኹኔታም ግን እያመቻቸ እንዳልሆነ ተገልጿል።

በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ በየዓመቱ የተሻለ የሥራ ዕድል ፍለጋ፣ ለሕገ ወጥ አስተላላፊዎች ሰለባ በሚኾኑበት አደጋ ባልተለየው ጉዞ ወደ አረብ አገሮች ያቀናሉ። ውሳኔውን የተቃወሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ ባለፈው ሳምንት፣ ከየመኗ ዋና ከተማ ዔደን ከሚገኘው የድርጅቱ ጽ/ቤት ደጃፍ ትዕይንተ ሕዝብ ማካሔዳቸውን ተከትሎ፣ ግጭት እንደተፈጠረና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችም እንደተገደሉ ተዘግቧል።

አቶ ቴዎድሮስ ትርፌ፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው፣ የዐማራ ተወላጆች መብቶች ተሟጋቹ “የዐማራ ማኅበር በአሜሪካ” የተባለው ድርጅት ሊቀ መንበር ናቸው። አቶ ቴዎድሮስ፣ ውሳኔው፥ የዐማራ እና የትግራይ ተወላጆች የኾኑ ስደተኞችን ለይቶ የተፈጸመ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተናጠል ያደረገው አግላይ ፖሊሲ ውጤት ነው፤ ይላሉ።

“እነኚኽ ኢትዮጵያውያን፣ ወደ አገራቸው ተመልሰው የመኖሪያ ቤት እና ሌሎች የሚያስፈልጓቸው አገልግሎቶች ተሰጥተዋቸው፣ በዐዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲኖሩ ሊደረጉ ይችላሉ። የዐማራ ተወላጆች በመኾናቸው ብቻ፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ ሊያቅታቸው አልያም የግድ ወደ ዐማራ ክልል መሔድ የለባቸውም። የዐማራ ተወላጆች፣ በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ይኖራሉ፤” ብለዋል።

በህወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በፕሪቶርያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት ተቋጭቷል፡፡ በአንጻሩ በሕዝብ ብዛቱ በአገሪቱ ሁለተኛ በኾነውና የፋኖ ታጣቂ በሚገኝበት የዐማራ ክልል፣ ሌላ ዐዲስ ግጭት መቀስቀሱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሐምሌ ወር መገባደጃ፣ በዐማራ ክልል በተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት፣ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው።

በ18 ዓመቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዘችው ሮማን፣ ምንም እንኳን የሥራ ዕድል ማግኘቱ ቢሳካላትም፣ ሥራ ለመሥራት የሚቻልበት ኹኔታ ግን እጅግ አዳጋች እንደ ነበር አስረድታለች። ዶር. መሳይ ሙሉጌታ፣ በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ናቸው። ዜጎች፣ አደገኛውን የስደት ጉዞ እንዳያደርጉ የማቀብ መፍትሔው፣ ኢኮኖሚያዊ ነው፤ ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ ሂዩማን ራይትስዎች በቅርቡ ያወጣው አንድ ዘገባ፣ የሳዑዲ አረቢያ ድንበር ጠባቂዎች፣ እ.አ.አ. ከመጋቢት 2022 እስከ ሰኔ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የየመንና የሳዑዲን ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንደገደሉ አመልክቷል።

የመብቶች ተሟጋቹ ቡድን አክሎም፣ ግድያዎች፣ በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች እንደሚቆጠሩ ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ የተባሉትን ግድያዎች ለማጣራት ምርመራ እንደሚያካሒድ ሲያስታውቅ፣ የሳዑዲ መንግሥት በአንጻሩ፣ ክሡን አስተባብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG