በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአገራዊ ምክክሩ ለሚሳተፉ የታጠቁ ኀይሎች የደኅንነት ጥበቃ እንደሚደረግ ኮሚሽኑ አስታወቀ


በአገራዊ ምክክሩ ለሚሳተፉ የታጠቁ ኀይሎች የደኅንነት ጥበቃ እንደሚደረግ ኮሚሽኑ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:03 0:00

ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ሒደቱ፣ በክልል ደረጃ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር የገለጸው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በምክክር ሒደቱ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ የታጠቁ ኀይሎች “የደኅንነት ጥበቃ እንደሚደረግ” አስታውቋል። ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምክክር ይጀመርባቸዋል ያሏቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች፣ የተሳታፊ ልየታ የተጠናቀቀባቸው ናቸው።

የእስከ አሁኑን የኮሚሽኑን የሥራ ክንውን ያደነቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤትም፣ በወቅታዊ ሀገራዊ የደኅንነት እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በመምከር፣ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ አገራዊ ምክክሩ፣ የኢትዮጵያን ነባር ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በመካሔድ ላይ ናቸው ካላቸው ተግባራት መካከል አንዱ መኾኑን ጠቅሷል።

በእያንዳንዱ ክልል “እጅግ ጥብቅ እና አድካሚ” ሲል የገለጸው ሥራ መከናወኑን በመግለጫው ላይ ያተተው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኮሚሽኑ በክልል ደረጃ የሚደረጉ የምክክር መድረኮችን ማካሔድ እንደሚጀመርም በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

እንደ መግለጫው፣ በአሁኑ ወቅት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ በ10 ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከየወረዳው በምክክሩ ሒደት የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ ተጠናቋል፤ በዚኽም “ከ679 ወረዳዎች 12ሺሕ294 ተሳታፊዎች ተለይተዋል፡፡”

የተሳታፊ ልየታው በተጠናቀቀባቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች በተዋረድ በሚደረገው ውይይት፣ አጀንዳ የመለየት ሥራ እንደሚከናወን፣ ዋና ኮሚሽነሩ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላት ወደ አገራዊ ምክክሩ ሒደት እንዲገቡ በድጋሚ ጥሪ ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ኮሚሽኑ በዐዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ፕር. መስፍን አርኣያ፣ ታጣቂዎችን ጨምሮ ጥያቄ ካላቸው ሌሎችም አካላት ጋራ ችግሮችን ለመፍታት፣ ኮሚሽኑ በአገር ውስጥም ይኹን ከአገር ውጭ ለመነጋገር ዝግጁ እንደኾነና ጥረትም በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኾኖም፣ ኮሚሽኑ እስከ አሁን በአካል አግኝቶ ያነጋገራቸው የታጠቁ አካላት ይኖሩ እንደኾን ላነሣንላቸው ጥያቄ፣ በጉዳዩ ላይ አሁን አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፣ ኮሚሽኑ ለአካታች ንግግር ያስተላለፈውን ጥሪ እንደሚያደንቅ አስታውቋል፡፡

ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሩ ኧርቪን ማሲንጋ፣ ዛሬ ረቡዕ ባወጡት አጭር መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ኹሉን አቀፍ ውይይት እንዲደረግ ያቀረበውን ጥሪ እንደሚደግፉ ገልጸው፣ “ገንቢ ምክክር ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት የተሻለው መንገድ ነው፤” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG