አንጋፋዎቹ ካድሬዎች ቀስ በቀስ እየለቀቁ መሆኑንም አምባሣደሩ አመልክተዋል፡፡
አሁን የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወጣትና ጥሩ ትምህርት ያላቸው፤ በሚኒስትርነት ቀደም ሲል በሠሩበት ዘርፍ ጉልህ ለውጥ ያስመዘገቡ፣ የኢትዮጵያንም የጤና ሁኔታና ገፅታ የለወጡ፣ የብዙ ሽልማቶች አሸናፊ የሆኑና በዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ በጤናው ዘርፍ ላይ ከሚሠሩ ተቋማት ብዙ ሙገሣን ያገኙ መሆናቸውን ዘርዝረዋል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት የተሾሙት ዶ/ር ከሠተብርሃን አድማሱም ከዚያው ከጤናው ዘርፍ የወጡ፣ ብዙ ልምድ ያላቸው፣ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ መሆናቸውን፣ ፓርቲው አይቶ የሾማቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የካቢኔው አደረጃጀት ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ያሉበት መሆኑ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኖር ከሚያዘው ሕገመንግሥት ጋር ይጋፋል የሚሉ ሰዎች እየተሰሙ መሆኑን እንዴት እንደሚያስተናግዱ የተጠየቁት አምባሣደር ዲና “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነው መሠረት ለተለያዩ የሥራ አስፈፃሚ ዘርፎች ኃላፊዎችን ይሾማል ከሚል በስተቀር በሕገመንግሥቱ ውስጥ የሠፈረ እንደዚያ የሚል ነገር የለም” ብለዋል፡፡
“በሃገሪቱ እየሰፋ የሚሄደውን እንቅስቄሴ ግምት ውስጥ በማስገባት ለተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ ኃላፊዎችን ማስቀመጥ አግባብ ይመስለኛል” ብለዋል ቃልአቀባዩ አክለው፡፡
የአሁኑ የካቢኔ አደረጃጀት ከአንድ ቡድን ቁጥጥር ለማስፋትና ከሃገሪቱ የተለያዩ ስብጥሮች ሰዎችን ለመሣብ የተሞከረ እንደሚመስል የሚያሳዩ ሹመቶች መኖራቸውን የአቶ ሙክታር አሕመድን ከኦሕዴድ፣ የአቶ ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን ከሕወሓት፣ የአቶ ደመቀ መኮንንን ከብአዴን መውጣት የሚጠቁም ይመስላል ተብለው የተጠየቁት አምባሣደር ዲና ሲመልሱ “በመሠረቱ በሃገሪቱ ውስጥ አንድ ቡድን አልነበረንም፤ በክልል ደረጃም ይሁን በፌደራል ደረጃ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተወከሉባት ፌደራል ሃገር ነች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሚያሣየው የበላይ አመራር አካሉ ቢያንስ ዋና ዋና የሚባሉ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተወከሉበት መሆኑን ነው፤ እንደጠቀስከው ኢሕአዴግ በአራት ድርጅቶች የተቋቋመ ግንባር ነው፤ እና አሁን ሁሉም ጀልባው ላይ ወጥቷል፤ ሁሉም ተካትቷል፡፡” ብለዋል፡፡
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡