የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ፣ የሐሰት ማኅበራዊ ሚዲያ ገፅ በመጠቀም በሕዝቦች መካከል ግጭትና ብጥብጥ እንዲፈጠር መረጃ ሲያሰራጩ ነበሩ ያላቸውን 29 ሰዎችን ማሰሩን ትላንት ሐሙስ አስታውቋል።
የታሳሪ ቤተሰቦችና የክልሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው ግለሰቦቹ የታሰሩት የአከባቢውን ባለሥልጣናት ስለነቀፉና በክልሉ አሉ ያሏቸውን ብልሹ አሠራሮችን ተችተው በስማቸው በተከፈተ ገፅ በመፃፋቸው እንጂ፣ "ሀሰተኛ ገፅ ተጠቅመው ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን አላስተላለፉም" ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ አስረድተዋል።
ቪኦኤ በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽንስ መምሕር እያየሁ ዓለምየሁ ርምጃው የሐሳብ ነፃነትን የሚገድብ መኾኑን ተናግረዋል።